“የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይቃረንም” አለማየሁ አንበሴ

“የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይቃረንም”

“-አማራው ፈላጭ ቆራጭ የሆነበት ስርአት ቢመጣ፣ እኔ ራሴ አምርሬ እታገለዋለሁ፡፡ ይሄ ትውልድ የነቃ ነው፡፡ አካሄዳችን የሰለጠነ የብሔርተኝነት ንቅናቄ ነው፡፡ ሃገር ለማፍረስ አልተደራጀንም፡፡--”

ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው ይባላል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ “የቀለም ቀንድ” ጋዜጣ ባለቤት የነበረው ሙሉቀን፤ የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እንዲጎላ ካደረጉ አክቲቪስቶች በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ 


በአማራ ህዝብ በደልና መገለል ላይ ያተኮሩ ሁለት ጥናታዊ መፅሐፍትም አሳትሟል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው በአማራ ክልል ሲካሄዱ የነበሩ ተቃውሞዎችን በመምራት ይታወቃል፡፡ ከሰሞኑም በአማራ ክልል መንግሥት ጋባዥነት በጥገኝነት ከሚኖርበት ስዊድን፣ ከ”ልሳነ አማራ” አዘጋጆች ጋር ወደ ሃገር ቤት ተመልሷል፡፡ 

በአሁኑ ወቅትም ከሌሎች ጋር በመሆን የአማራ ህዝብን የሚወክል የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው፤ ስለ አማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ፣ የአማራ ብሔርተኝነት እንዴት ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንደሚታረቅ፣ የአማራ ህዝብ የደረሰበት በደሎች ላይ ስላደረገው ጥናት፣ በአገሪቱ እየታየ ስላለው ለውጥና ብአዴን ስለሚገኝበት ፖለቲካዊ ቁመና እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

እንዴት ነው ወደ ጋዜጠኝነትና አክቲቪስትነት የገባኸው?

ወደ ሚዲያ ሥራ የገባሁበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እኔ በዩኒቨርሲተ ያጠናሁት ስነ ልቦና ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በሚዲያ ላይ የመስራት ፍላጎቴ ከፍተኛ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ የንባብ ባህሉ አለኝ፡፡ ብዙ ጊዜዬን የማጠፋው በንባብ ነበር፡፡ በኋላም ወደ ጽሑፍ ገብቼ የተለያዩ ታሪኮችን፣ ሁነቶችን በማስታወሻዬ መመዝገብ ያዝኩ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሆኜም ፅሁፎቼን ለተለያዩ ጋዜጦች እየላክሁ ታትመው ይወጡልኝ ነበር፡፡ 

ሌላው እኔ ያደግሁት ተመሳሳይ ባህልና ቋንቋ በሚናገር ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ደግሞ የገጠመኝ የተለየ ነገር ነው፡፡ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል ነው ያጋጠመኝ፡፡ ያ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች እኔ ስለመጣሁበት የአማራ ህዝብ ጉዳይ ብዙ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ 

ብሔር ብሔረሰብ ሲባል የአማራው ጉዳይ ብዙም ትኩረት አያገኝም። ያ ለእኔ ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር፡፡ ስለ አማራ ጉዳይ ጋዜጠኞች እንኳ በአግባቡ ዘገባ አያቀርቡም፡፡ ስለ ሌላው ብሔረሰብ በድፍረት በየጋዜጦቹ ሲፃፍ ስለ አማራ ግን አይጻፍም ነበር፡፡ እንደውም የአማራ ስም እንዲነሳ የማይፈልጉ ሁሉ የነበሩ ይመስላል፡፡ 

በ2008 ከቤኒሻንጉልና ከጉራፈርዳ አማራዎች ሲፈናቀሉ፣ የረባ ዘገባ እንኳ አልቀረበም፡፡ እኔ በወቅቱ ተፈናቃዮች ወደተጠለሉበት ቦታ ሄጄ፣ መረጃዎች አሰባስቤ ለሚዲያዎች ብልክም ደፍሮ የሚዘግበው አልተገኘም ነበር፡፡ የአማራው ጉዳይ በዚህች ሃገር ውስጥ ቸል የተባለ መሆኑን የበለጠ የተረዳሁት ያኔ ነው፡፡ 

የራሴንም ጋዜጣ እስከ ማቋቋም ያደረሰኝ ይሄ ሁኔታ ነው፡፡ በተለይ በአማራው ላይ የሚደርሱ ግፎች፣ መገለሎች በሚዲያዎች ትኩረት አለማግኘቱ የበለጠ ድምፅ ለመሆን አነሳስቶኛል። ወደ ሚዲያ ስራ የመጣሁት ለዓላማ ነበር፡፡ በየቦታው በደል ለሚፈፀምበት የአማራ ህዝብ ድምፅ ለመሆን ነው፡፡ 

“የቀለም ቀንድ” ጋዜጣን የመሰረትከው ለዚህ ዓላማ ነበር ማለት ነው?

በመጀመሪያ ባህር ዳር ነበር የምኖረው፡፡ ስራዬም በአብዛኛው ከማህበረሰቡ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘን ነበር፡፡ በየቀኑ በማህበረሰቡ እየተጋፈጣቸው ያሉ ችግሮችን እመለከት ነበር። እነሱን ዝም ብዬ በማስታወሻዬ እየመዘገብኩ አስቀምጥ ነበር፡፡ የተቀጠርኩበትን ስራዬን እየሰራሁ፣ በጎን በማስታወሻዬ መረጃ እያሰባሰብኩ ቆየሁ፡፡ 

አዲስ አበባ ላሉ የተለያዩ ጋዜጦች ፅሁፌን እልክ ነበር፡፡ በአብዛኛው ፅሁፌን ያወጡታል፡፡ በኋላ “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ላይ ቋሚ አምደኛ ሆኜ፣ ከባህር ዳር በተለይ የአማራውን ጉዳይ የተመለከቱ ፅሁፎችን እፅፍ ነበር፡፡ ዘገባዎችን እልክ ነበር፡፡ በኋላ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው በሙሉ ዝግጅት ገባሁ፡፡ 

ፅሁፎች እፅፍ ነበር፡፡ ሰዎች ፅሁፎቼንና ዘገባዎቼን ይወዷቸው ነበር፡፡ እኔም ራሴን የበለጠ ለማብቃት መፅሐፍትን በሚገባ ማንበብ ያዝኩ። “የቀለም ቀንድ” የተፈጠረችው ከእነዚህ ሂደቶች በኋለ ነው፡፡ በተለይ የአማራውን ጉዳይ የሚዘግቡ ሚዲያዎች፣ ጋዜጦች ሲጠፋ አሁን አሜሪካን አገር ካለው ሸንቁጥ አየለ ጋር ሆነን፣ ለምን ለዚህ ህዝብ ድምፅ የሚሆን ጋዜጣ አንጀምርም በሚል ሃሳብ ነው የጀመርነው፡፡ በዋናነት ስለ አማራ መገለል ብንዘግብም ሌሎች ጉዳዮችንም እናስተናግድ ነበር፡፡

የአማራው ጉዳይ እረፍት ስለሚነሳኝ በመሃል “የክፉ ሰው ሽንት” የተሰኘች መፅሐፍ አሳተምኩ። ስለ አማራው መገለል በማስረጃ የምትተነትን መፅሐፍ ነች፡፡ ስለ አማራ መናገር ብዙም ተቀባይነት በሌለው ጊዜ የታተመች መፅሐፍ ብትሆንም ግብረ መልሱ ከጠበቅሁት በላይ የበለጠ በማህበረሰቡ ጉዳይ ጊዜ ወስጄ እንድሰራ ያበረታታኝ ነበር፡፡ 

መፅሐፏ ሁሉንም ሽፍንፍን የገለጠችና ዝምታውን የሰበረች ነች፡፡ በአማራው አካባቢ በሰፊው መነጋገሪያ ሆና ነበር። “የቀለም ቀንድ” ጋዜጣ ደግሞ የመጀመሪያዎቹን 7 እትሞች እንደሄድን፣ ገበያውንና የመንግስትን ጫና ስላልቻልነው 2007 ላይ አቋረጥናት፡፡ ብዙዎች የዘረኞች ጋዜጣ እያሉ ያብጠለጥሏት ነበር፡፡ 

ምርጫ 2007 አካባቢ ነገሮች አዝማሚያቸው አላምር ሲለኝ፣ ወደ ጣና ቂርቆስ ገዳም ሄጄ፣ በዚያ ከሁለት ሳምንት በላይ የጥሞና ጊዜ ለመውሰድ ተቀምጫለሁ፡፡ ጥሩ የጥሞና ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከገዳሙ ስወጣ “ግንቦት 7ን ኤርትራ ሄዶ ሊቀላቀል ነው” ተብዬ በወታደር ከበባ ተፈፅሞብኝ ነበር፡፡ 

ያረፍኩበት ሆቴል ተከቦ፣ ስልኬን አጥፍቼ እንድቀመጥ ተገድጄ ነበር። በኋላ በራሳቸው ጊዜ ትተውኝ ሄዱ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩኝና 2008 ላይ ጋዜጣዋን እንደገና ጀመርኩ። ጋዜጣዋን በድጋሚ ስጀምር ግን ጋዜጣዋን ለመሸጥ በማሰብ አልነበረም፡፡ 

በመላ ኢትዮጵያ የሚገኘው የአማራ ህዝብ ላይ ለማካሄድ ላሰብኩት ጥናት ሽፋን እንዲሆነኝ ነበር፡፡ ዋነኛ አላማዬ አማራው ላይ የደረሰውን በደል ፈልፍሎ ማውጣት ነበር፡፡ ከጋምቤላ በስተቀር ለጥናት ያልሄድኩበት የሃገሪቱ ክፍል የለም፡፡ አማራ አለ በተባለበት ቦታ ሁሉ ተዘዋውሬ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። 

በዚህ ጉዞዬ ግን የጋዜጣዋን የትብብር ደብዳቤ ይዤ ነበር የምንቀሳቀሰው። በዋናነት ጋዜጣዋን እንደገና የከፈትኩት ለዚህ ሽፋን ነበር። ለሁለት ዓመት በዚህ መልኩ ጥናቱን ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊት የሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ትምህርቴን ሳጠናቀቅ የመመረቂያ ጽሁፌን የሰራሁትም በዚሁ በአማራው መገፋት ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ 

በማህበረሰባዊ ሥነ ልቦና (ሶሻል ሳይኮሎጂ) ነው የተመረቅሁት። በጥናቱ በዋናነት የአማራ ማህበረሰቦች ከየቦታው ከተፈናቀሉ በኋላ የሚገጥማቸው ሥነ ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውስ ምንድን ነው? በሚለው ላይ ነው አተኩሬ ያጠናሁት። “የዘመኑ ጥፋት” መፅሐፌም ለሁለት ዓመታት ባካሄድኩት አድካሚ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ 

ጥናቱን ሳጠናቀቅና የአማራው ተጋድሎ ሊጀመር እንደሆነ ሳውቅ፣ ጋዜጣዋን ዘግቼ ለህዝቡ የበለጠ ድምፅ የምሆነውና ተጋድሎው ግቡን እንዲመታ ማድረግ የሚቻለው እዚህ ተቀምጦ በመታሰር ሳይሆን ወጥቶ ድምፅ በመሆን ነው በሚል ወደ አውሮፓ ሄድኩ፡፡ የሄድኩበት አጋጣሚ የዓለም የፕሬስ ቀን ይከበር ስለነበር በዚያ ላይ ተጋብዤ ነው፡፡ 

ብዙ ወዳጆቼ ወደ ሃገር ቤት መመለስ የለብህም፣ ተጋድሎውን ማገዝ አለብህ አሉኝ፡፡ እኔም ያመንኩበት ጉዳይ ስለነበር በዚያው ጥገኝነት ጠይቄ ቀረሁ፡፡ 

በዚህ ጥናት ወቅት በዋናነት የገጠመህ ተግዳሮት ምን ነበር?

እኔ ያደግሁት ስለ ኢትዮጵያ ብቻ አውቄ ነው። ለምሳሌ በት/ቤታችን የአማራ ክልል መዝሙርን ዘምሩ እንባላለን፡፡ እኛ ግን የአማራን መዝሙር አንዘምርም፣ የኢትዮጵያን እንጂ ብለን አሻፈረን እንል ነበር። መምህራን አይሆንም፣ የአማራ ክልልን መዝሙር ዘምሩ ብለው ሲያስገድዱን፣ በህብረት አባታችን ሆይ የሚለውን ፀሎት ፀልየን ወደ ክፍል እንገባ ነበር። ያን ያህል ነበር ለኢትዮጵያዊነት ያለን ትርጉም፡፡  

ውስጤ የነበረው አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው። ሌላ ነገር አልነበረም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ግን ሃገሪቱ እኔ በልጅነቴ የማውቃት አይደለችም። በልጅነቴ የሳልኳትን ሃገር ዩኒቨርሲቲ ስገባ ላገኛት አልቻልኩም፡፡ ከዚያም አልፎ በዘር ምክንያት በግልፅ በደል ሲፈፀም እመለከት ነበር፡፡ 

ስሜን ብቻ አይተው የአማራ ስም ሲሆን መምህራን በውጤቴ ላይ ሆን ብለው ተፅዕኖ ይፈጥሩብኝ ነበር፡፡ ይሄ በግልፅ እኔ ማን ነኝ? ብዬ እንድጠይቅ ነው ያስገደደኝ፡፡ በዩኒቨርሲቲ የማየው የብሄር መድልኦ፣ ብዙ ጥያቄ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት አመራር አባል ነበርኩ፡፡ 

የተሻለ ኢንተርኔት የማግኘት እድል ነበረኝ፡፡ በዚያ በመጠቀም የተለያዩ መፅሐፍትን አነብ ነበር፡፡ በኋላ ስለ ፕ/ር አስራት ወልደየስ የእስር ሁኔታ አነበብኩ፡፡ በኋላም በእስር ቤቶች ውስጥ ያለ የታራሚዎችን ጭንቀት የሚለካ ጥናት በጅማ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ላይ መስራት ጀመርኩ፡፡ 

በማረሚያ ቤቱ በብሔራቸው ማንነት ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩ ታራሚዎችን አገኘሁ፡፡ ጥቃት የሚያደርሱ የመኖራቸውን ያህል፣ በዚያው ልክ ጥሩ የሚያስቡ የብሔር ጥቃት የሚጠየፉ አሉ፡፡ ይሄ የምልከታ ጥናት የበለጠ ነገሩን ገፍቼ እንድቀጥል ገፋፋኝ፡፡ 

ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉና ፍኖተ ሰላም ተጠልለው የነበሩትንም በቦታው ተገኝቼ ከተመለከትኩ በኋላ መደበኛ ስራዬን ለመተው ያደረሰኝ መረበሽ ውስጥ ነው የገባሁት። በዚህ የጥናት ጊዜ ውስጥ ብዙ ለህይወቴ አደጋ የሆኑ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ በጣም ተግዳሮት የበዛበት ነበር፡፡ 

ራሴን በተለያዩ መንገዶች እየለወጥኩ ነበር ከቦታ ቦታ እየዞርኩ መጠይቅ ስሰራ የነበረው፡፡ የሚገርመው ከተጎጂዎቹ ከራሳቸውም ተግዳሮት ይገጥመኝ ነበር፡፡ “እንደገና ልታስፈጀን ነው ወይ” እያሉ ይሸሹኝ ነበር፡፡ እንደ ሰላይም እያዩ በጥርጣሬ ይመለከቱኝ ነበር፡፡ በዚህ በጣም ተፈትኛለሁ፡፡ 

በጥናትህ ይፋ ላደረግኸው ጥፋት እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አለ? አጥፊዎች ለህግ የሚቀርቡበት ዕድልስ የለም?
በየትኛውም ሁኔታ ጨፍጫፊዎች ጨፍጭፈናል ብለው እውቅና አይሰጡም፡፡ በሩዋንዳ በተደረገው ጭፍጨፋ፣ ጨፍጭፈናል ብለው ራሳቸውን ይፋ ያደረጉ የሉም፡፡ አብዛኞቹ በፍ/ቤት ተፈረደባቸው እንጂ እኛ ፈፅመነዋል ብለው አላመኑም፡፡ ጉዳዩ ከዘር ማጥፋት ጋር ተያይዞ የሚታይ ስለሆነ ዛሬ በወቅቱ የኦነግ አመራር የነበሩ ሰዎች እጃችን የለበትም ብለው ራሳቸውን ቢያሸሹ ሊገርመን አይገባም፡፡ 

እኔም ሆንኩ በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያለን ሰዎች፤ በቀልን አንደግፍም እንዲኖርም አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ያጠፉ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ያ የዘር ጭፍጨፋ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ አንዱ የኛ ትግል፣ የዘር ጭፍጨፋው እውቅና እንዲያገኝ ነው። እውቅና አግኝቶ ቂም በቀል ቀጣይነት እንዳይኖረው፣ ማስተማሪያ መሆን አለበት፡፡

እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች ገለልተኛ የተባሉ አካላት ጉዳዩን እንደገና እንዲያጠኑት ማድረግም ይቻላል፡፡ እንደገና ቢጠና በኔ መፅሐፍ ከወጣው የበለጠ ብዙ ጉድ እንደሚወጣ እርግጠኛ ነኝ። የኔ ከውቅያኖስ ውስጥ ትንሽ ጠብታ እንደ መጨለፍ ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ጎልቶ የወጣባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የአማራ ብሔርተኝነት ዛሬ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው በአማራው ላይ የደረሰው ግፍ፣ በደል፣ ማንነቱን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ጭፍጨፋ፣ መፈናቀልና እንግልት ነው፡፡ ብሔርተኝነት አንድ ህዝብ እስካለ ድረስ የሚኖር ዘላለማዊ ጉዳይ ነው፡፡ 

ብሔርተኝነትን እኔ የምረዳው፤ አለሁበት፣ ከውስጡ ወጥቻለሁ፣ በባህሉ በሥነ ልቦናው ኮትኩቶ አሳድጎኛል ስለምንለው ማህበረሰብ መቆርቆር ነው፡፡ ለምሳሌ የአማራ ህዝብ እስካለ ድረስ ለአማራ ህዝብ ተቆርቋሪነት ይኖራል። ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት ይኖል። ሰፋ አድርገን አፍሪካዊ ነን ስንል ደግሞ የአፍሪካዊነት ብሔርተኝነት አለ፤ በቃል እንጂ በተግባር ማንም ሰው ብሔርተኛ ነው፡፡ 

ብሔርተኛ ከመሆን አይድንም፡፡ በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔርተኝነት ለምን ጎልቶ ወጣ ለሚለው ጥያቄህ፣ አማራውን መሰረት ያደረገ ግፍና በደል በተለይ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1928 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ስላልቆመ ነው። ጣሊያን የአማራን ህዝብ መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ አድርጓል፡፡ 

ይሄን የእነ ካምቤል የእነ አልቤርቶ ሴባኪን እና የሌሎችን መፅሐፍ በማንበብ መረዳት ይቻላል። መፅሐፎቹ አማራው በወቅቱ ምን ያህል ግፍ እንደደረሰበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ በተለይ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በአማራ ህዝብ ላይ ብዙ ጥፋት ተፈፅሟል፡፡ ከደርግ ጀምሮ የአማራ ህዝብ ቁጥርን በማሳነስ የሚደረገው ጥፋት አንዱ ግፍ ነው፡፡

የሕዝቡን ቁጥር ሆን ብሎ የሚያሳንሱ ናቸው ከመንግሥት የሚወጡት አሃዞች፡፡ ለምሳሌ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን “Greater Ethiopia”ን ሲፅፍ እ.ኤ.አ በ1972 በሃገሪቱ 10 ሚሊዮን አማራ፣ 7 ሚሊዮን ኦሮሞ ብሏል፡፡ በኋላስ እ.ኤ.አ በ1984 በተደረገ የህዝብ ቆጠራ ደርግ ሆን ብሎ የአማራውን ቁጥር በማሳነስ አንደኛ ኦሮሞ፣ ሁለተኛ አማራውን አደረገ፡፡ 

ኢህአዴግ ደግሞ የበለጠ ፀረ አማራ አቋም ስለነበረው በብዙ እጥፍ ህዝቡን በማሳነስ አቅርቧል፡፡ እነዚህ ሁሉ በደሎች ለማህበረሰቡ በቀላሉ የሚታዩ አይደለም፡፡ 

የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴን እንደ ስጋት የሚመለከቱት ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?

እኔ ለተገፋው ህዝብ ድምፅ ለመሆን የምጥር ሰው ነኝ፡፡ ከአማራ ህዝብ እንደወጣ አንድ ግለሰብ እንጂ ህዝቡን አልወክልም፡፡ በመሰረቱ የአማራን ብሄርተኝነት ሌሎቹን ያገለለ ወይም ገፊ አድርጎ መመልከትም ትክክል አይደለም፡፡ እንቅስቃሴው በማለቃቀስ ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ የሰለጠነ ብሔርተኝነት ነው፣ ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ የሰለጠነ ብሔርተኝነት ከዲሞክራሲ ጋር አይፃረርም፡፡ 

እኛ የምንፈልገው አንዱ የበላይ፣ አንዱ ተገፊ፣ አንዱ የበታች የማይሆንበት ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ ነው፡፡ ለአበበም፣ ለገመቹም፣ ለሃጎስም ለሌላውም እኩል የሆነ አስተዳደር እንዲፈጠር ነው የምንታገለው፡፡ ማንም በቋንቋውና በማንነቱ እንዲሰደድ፣ እንዲገደል አንፈልግም፡፡ 

ለምሳሌ እኔ በምኖርበት አውሮፓ የመንግስት አገልግሎት ስፈልግ፣ የአማርኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ተፈልጎልኝ፣ አገልግሎቱን ያለ ብዙ ድካም አገኛለሁ፡፡ ነገር ግን የእዚሁ ሃገር ዜጋ ሆነው አማርኛ የሃገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሳለ፣በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ማግኘት ሳይችሉ፣ ፍትህ ማግኘት የተሳናቸው ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ አንድን የፍ/ቤት ወረቀት ከአማርኛ ወደ ሌላ ቋንቋ ለማስተርጎም በአንድ ገፅ እስከ መቶ ብር የሚጠየቁ ገበሬዎች አሉ፡፡ 

ይሄ ፍትሃዊ ነው? ይሄ ተገቢ ነው? ይሄን የሚፈጽሙና ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ናቸው ዛሬ የአማራው መደራጀት የሚያሰጋቸው እንጂ አማራ ተደራጅቶ ሌላውን ሊጎዳ አይችልም፡፡ እኛ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ስርአት እንዲመጣ ፈፅሞ አንፈልግም፡፡ አማራው ፈላጭ ቆራጭ የሆነበት ስርአት ቢመጣ፣ እኔ ራሴ አምርሬ እታገለዋለሁ፡፡ ይሄ ትውልድ የነቃ ነው። አካሄዳችን የሰለጠነ የብሔርተኝነት ንቅናቄ ነው፡፡ 

ሃገር ለማፍረስ አልተደራጀንም፡፡ ሃገር ለማፍረስ የአማራ ብሔርተኝነትን አልጀመርንም። በዚያው ልክ እኛ የተለየን የዚህች ሀገር ጠባቂ ነን ብለንም አናስብም። ጨቋኞች ናቸው በአማራው ብሔርተኝት ሊሸበሩ የሚችሉት፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ማህበረሰቡ የበለጠ ለመብቱ እንዲታገልና የመጣው አንፃራዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ከማድረግ ውጪ እስከ አሁን ያደረሰው ጉዳት የለም፡፡  ለወደፊትም አይኖርም፡፡ የሰለጠነ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያዊነት እና የአማራ ብሔርተኝነትን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?

የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ተቃርኖ የቆመ አይደለም፡፡ አማራው አማራ ነኝ በማለቱ ከኢትዮጵያ ላይ የጎደለ ነገር የለም፡፡ እንደውም የጨመረው ነገር አለ፡፡ አማራው በአማራነቱ ተደራጅቶ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፈጠረውን ነገር ሁላችንም የምናየው ነው፡፡  

አማራው በማንነቴ ተጠቃሁ ብሎ ተጋድሎውን ሲጀምር ነው ለውጡ ተፈጥሮ እውን የሆነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ማንሳቱ መነሻው ነው፡፡ በዚህ ንቅናቄ የአማራው ብሔርተኝነት የበለጠ ኢትዮጵያን አስቀጥሏል፡፡ አማራነት አለ፣ ኢትዮጵያዊነት አለ፣ ከኢትዮጵያዊነት አልፎም አፍሪካዊነት አለ፡፡ በዚህ መንገድ ነው የምንንቀሳቀሰው። የአማራ ብሔርተኛነት ከኢትዮጵያዊነት የተቃረነ አይደለም፡፡ 

ለአማራ ህዝብ መበደል ክልሉን ሲመራ የኖረውን ብአዴንን ተወቃሽ ታደርጉታላችሁ… የቀድሞውንና የአሁኑን ብአዴን እንዴት ትገልጸዋለህ?

በመሰረቱ ብአዴን ራሱን ባይቀይር ኖሮ እስካሁን መቀጠል አይችልም ነበር፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፈጠረውን ማህበረሰባዊ መነቃቃት በግልፅ እያየነው ነው፡፡ አሁን ያሉት መነቃቃቶችና ለውጦች ጥሩ ናቸው፡፡ አሁንም ግን ብዙ ይቀራል፡፡ የትርክት ለውጥ ያስፈልጋል። 

በብአዴን ውስጥ የነበሩ ፀረ አማራ አቋሞችና ትርክቶች በሙሉ ተተችተው መራገፍ አለባቸው። በትክክል የአማራውን ህዝብ በሚገልፁና ተጠቃሚ በሚያደርጉ መሰረቶች ላይ እንዲቆም ያስፈልጋል፡፡ የአማራን ህዝብ እየመራ እስከሆነ ድረስ ብአዴን ራሱን የበለጠ ማስተካከል አለበት። ካላስተካከለ ወጣቱ በቸልታ አይመለከተውም። 

አሁን ህብረተሰቡ ለመረጃ ቅርብ ሆኗል፡፡ ብአዴን እነዚህን ታሳቢ አድርጎ ራሱን ሙሉ በሙሉ ማፅዳት አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ አመራሮቹ ቀናዎች ናቸው፡፡ ለህዝብ ተቆርቋሪ እንደሆኑ ያስታውቃሉ። ነገር ግን በተግባር መፈተን አለባቸው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ እንዴት ትመለከተዋለህ?

አሁን ባለው ለውጥ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አሉ። እነዚህን ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች ዝም ካልናቸው ግን ተመልሰው የሚዳፈኑበት ሁኔታም ይኖራል። ስለዚህ አክቲቪስቱም የፖለቲካ ሰዎችም የሚዲያ ባለሙያዎችም ደጋግመው መንግስትን እየተቹ፣ ለውጡን ህዝቡ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ማስኬድ ያስፈልጋል፡፡ 

የሆነ ለውጥ ስለመጣ ብቻ ከመንግስት ጋር ማጨብጨብ ለለውጥ አጋዥ አይሆንም። ጉድለቶችን ነቅሶ መተቸት ያስፈልጋል፡፡ እንደኛ አይነቱ አክቲቪስት፣ ደግ ተቺ እንጂ አጨብጫቢ መሆን የለበትም፡፡ 

ሁልጊዜ የማህበረሰቡን ችግር እየተመለከትን እንዲስተካከል መተቸት ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላ የአማራ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆናን አይሸከምም፡፡ መንግስት ወዶም ይሁን ተገዶ ዜጎች ወደሚፈልጉት አቅጣጫ በመሄድ ቀድሞ ጭምር መገኘት አለበት፡፡  

አሁን አንፃራዊ ለውጥና ነፃነት አለ። በዚያው ልክ ዜጎች አሁንም ይፈናቀላሉ፤ ይገደላሉ። የማዕከላዊ መንግስቱ ሚናም የደከመ ይመስለኛል፡፡ የፌደራል መንግስቱ መጠናከር አለበት፡፡

Post a Comment

0 Comments