ከ3 ዓመት በኋላ ነፃ የወጣው ፊልም - ናፍቆት ዮሴፍ



ከ3 ዓመት በኋላ ነፃ የወጣው ፊልም

  • “በታሪካችን፤ በሙዚቃ እንጂ በፊልምና በቲያትር የተቀሰቀሰ አብዮት የለም”

  • “ፊልሞች ሳንሱር የሚደረጉት በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ብቻ ነበር”
“እሾሃማ ፍቅር” የተሰኘ ፊልሙን በ1994 ዓ.ም ፅፎ በማዘጋጀት ነበር የፊልም ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው፡፡ በመቀጠልም “ላገባ ነው” የሚል ወደ ኮሜዲ ዘውግ የተጠጋና በርካቶች የወደዱለትን ፊልም ለመስራት ችሏል፡፡ በቀንዲል ቤተ-ተውኔት፣ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በተዋናይነትም ሰርቷል - የዛሬው እንግዳችን ተዋናይና የፊልም ባለሙያ ሐብታሙ ማሞ።

“ሀብታሙ ማሞ ከሆነ ቦታ” በሚል በፌስቡክ ገፁ ላይ በሚፅፋቸው መሳጭ ግጥሞችም ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ፊልሞች ላይ በረዳት አዘጋጅነትና በተዋናይነት የተሳተፈው ሃብታሙ፤ “ታስጨርሽኛለሽ ቁጥር 1” የተሰኘ ፊልም ሰርቶ ተቀባይነት ያተረፈ ቢሆንም፣ የዚህ ፊልም ተከታይ የሆነው “ታስጨርሽኛለሽ 2” በሳንሱር ምክንያት ታግዶ፣ ለዓመታት ሲሟገት መቆየቱን ይገልጻል፡፡

ባለፈው ሳምንት ግን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ያልተጠበቀ ዜና አብስሯል፡፡ ለዓመታት በፊልም ሥራዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረው ቅድመ-ምርመራ (ሳንሱር) መቅረቱን ቢሮው ይፋ አድርጓል፡፡ ይሄን ተከትሎም ለ3 ዓመታት ታግዶ የቆየው የሃብታሙ ማሞ “ታስጨርሽኛለሽ 2” ፊልም ነጻ ወጥቷል። 

አሁን የእሱ ፊልም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፊልም ጥበቡ ነጻነቱን ያወጀ ይመስላል - ከሳንሱር መቀስ። ለመሆኑ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ለዓመታት በብቸኝነት ሲተገብረው የቆየውን የሳንሱር አሰራር፣ እንዴት ለማስቀረት ወሰነ? የሀብታሙን ፊልም ከዕይታ ያሳገደው ምን ነበር? የሳንሱሩ መነሳት ለፊልም ኢንዱስትሪው ምን ትርጉም አለው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አርቲስት ሀብታሙ ማሞን በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡ እነሆ፡-

መቼ ነው “ታስጨርሽኛለሽ- አንድ” የተሰኘውን ፊልም ለዕይታ ያበቃኸው?
መጀመሪያ የሰራሁት “ላገባ ነው” የሚለውን ፊልም ነበር፡፡ “ዌይተሩ”፣ “ሜድ ኢን ቻይና”፣ “የምሽቱ ፍፃሜ” የተሰኙ ፊልሞች ላይ በረዳት አዘጋጅነትና በትወና ሰርቼአለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው “ታስጨርሽኛለሽ 1”ን የሰራሁት፡፡ ፊልሙ እንደምታስታውሺው፤ በባህሪው ተምሳሌታዊ (“ሲምቦሊክ”) ነው፡፡ እያንዳንዱ ተዋናይ፤ እያንዳንዱ ቃለ ተውኔትና የታሪክ ግጭት ጠቅላላ ምክንያታዊና በሲምቦል የተወከሉ ናቸው፡፡ 

ለምሳሌ የትህትናን ገፀ ባህሪ ብንመለከት፣ ኢትዮጵያን የመወከል አይነት ነው፡፡ ቶማስ ቶራ (የጀነራሉን) ገፀ ባህሪ ብታይው፣ የቀድሞውን ሥርዓት፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማስከበር የተከፈለውን መስዋዕትነትና ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች ሲወክል፤ እነ ነፃነት የሰሩትን ክፍል ስታይው ደግሞ የግዴለሽነትና የምንቸገረኝ መንፈስ የተጠናወተውን የአሁኑን ትውልድ ያሳያል፡፡ 

አይጧን ካስታወስሻት፣ በእኛ ባህል አይጥ ምቀኛ ነው የምትባለው፡፡ ስለዚህ አይጧ ለኢትዮጵያ እንደ ምቀኛ፣ እንደ እንቅፋት-- ሲምቦል የተደረገች ናት፡፡ የእድገታችን፣ የአንድነታችን፣ የፍቅራችን፣ የመተሳሰባችን-- እንቅፋት ተደርጋ ነው የተቀረፀችው፡፡ ፊልሙ በአጠቃላይ ዘመናችንን የሚቃኝ ነበር፡፡

“ታስጨርሽኛለሽ 2”ን ለመታገድ ያበቃው በዋናነት ምን ነበር?
“ታስጨርሽኛለሽ 2” የቁጥር አንዱ ተከታይ ነው። ነገር ግን በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶቻችን ላይ እየተሳለቀ፣ እንከኖቻችንን እየነቀሰ እያወጣ የሚያሳይ ነው። እንከኖቻችንን መንቀስና መሳለቅ ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻችን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም የሚያመላክት ነበር፡፡ ፊልሙ ተሰርቶ የተጠናቀቀው በ2007 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ሲሰራ፣ ከውሻ ጋር ነበር፡፡  

በጣም አድካሚ ቀረፃ ነበረው፡፡ የእኛ ፊልም ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ማለትም፣ 2007 ዓ.ም ግንቦት ላይ አገራችን ብሔራዊ ምርጫ ላይ ነበረች፡፡ ያጋጣሚ ነገር ሆኖ ይሁን አላውቅም፣ የፊልሙ ዋነኛ ጭብጥ፤ ፍትሃዊ ምርጫ ላይ ያጠነጥናል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ ከ2007 ምርጫ ጋር ተያይዞ፣ የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ለማጋጋልም ለማባባስም ታስቦ የተሰራ ፊልም አይደለም፡፡ 

ነገር ግን በአንድ አገር ውስጥ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ። በዛ የፊልም ሲን ውስጥ የተወከለችው ሴት ናት፡፡ የግል ተፎካካሪ ፓርቲን ወክላ ነው የምትወዳደረው፡፡ የቅስቀሳዋ ስልት ራሱ የኮሜዲ ክፍል ያለውና ሥሜት የሚገዛ ነው፡፡ አንደኛ፤ ስለ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማንሳት ጊዜና ወቅት ይገድበዋል ብዬ አላምንም፡፡ በየጊዜው የሆነ ሥርዓት ይመጣል፡፡  

የዚያ ስርዓት አስተሳሰብ ሲያረጅ፣በሌላ አዲስና መልካም አስተሳሰብ ለመተካት፣ ዜጎች የራሳቸውን አዳዲስ አሳቢ መሪዎች የሚመርጡበት ሥርዓት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ አገራችን በሁለት ባላ ላይ ተወጥራ ባለችበት---አገሩን የሚመራው አካል፣ የአሳዳጅና ተሳዳጅ ድራማ በሚጫወትበት ሰዓት … ከእኛ ፊልም ጋር ተገጣጠመ፡፡

እርግጥ የተቆረጡ ክፍሎች ነበሩት፡፡ “ምንድነው… ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ አሸንፋለሁ ብሎ ያስባል? እንዴት አንድ ሰው እንኳን እኛን ተፎካካሪዎችን አይመርጠንም” … እያለ የሚሞግት የፊልሙ ክፍል አለ። የአገሪቱ የምርጫ ውጤት ሲገለፅ፤ 99 በመቶ ምናምን ተባለ፡፡ የእኛ ፊልም ልክ እንደ ትንቢት ነጋሪ ሆነ፡፡ ፊልሙ ላይ ብዙ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው ፊልሞቹን የሚገመግመው፡፡ ለመታገዱ ምን ምክንያት ነው የሰጣችሁ?
ትክክል ነው፡፡ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው ያገደው፡፡ በጣም የሚገርመው፣ የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ጊዜ ፊልምን ሳንሱር አድርጎ አያውቅም፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ አንድ እና ሁለት ላይ፣ የህዝቦች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በግልፅ ተደንግጓል፡፡ 

ይህን በህግ የተቀመጠ መብት ሲጥስና ሲደፈጥጥ የነበረው፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው፡፡ ደቡብ፣ ትግራይ፣ አማራ ክልል ብትሄጂ … የነዚህ ክልሎች ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ አንድም ፊልም ሳንሱር አድርገው አያውቁም፡፡

ሳንሱር እንደማያደርጉ እንዴት እርግጠኛ ሆንክ…?
በተለያዩ ክልሎች ለፊልም ስራ እንቀሳቀሳለሁ። ሐቃሳ ቱርሚ ፊልም ኮሌጅ፣ ፊልም አስተምር ነበረ። ፊልም ለማሳየት በተለያዩ ክልሎች እንዞራለን። ለምሳሌ አዲስ አበባ የተገመገመም ያልተገመገመም ፊልም ይዤ ኦሮሚያ ሄጄ አሳይቻለሁ፡፡ ማንም ተገምግሟል አልተገመገመም ብሎ የጠየቀኝ፣ ያጉላላኝ አካል የለም።  

ክልል ላይ የተሰሩ ፊልሞችን አዲስ አበባ ማሳየት ከፈለጉ፣ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መጥተው ነው የሚያስገመግሙት እንጂ የክልላቸው ቢሮ አይገመግምም፤ አይጠይቃቸውም፡፡ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በቋሚነት ቀደም ሲል በማዘጋጃ ቤት፣ በኋላ ደግሞ በራሱ ቢሮ ተቋቁሞ ሳንሱር ሲያደርግ ቆይቷል። 

ሳንሱር የሚያደርጉባቸው መስፈርቶች፤ “መሰረታዊ መዝናኛና ማስተማርን በማይፃረር…” በሚል ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ባልተፃፈ ህግ፤ ፖለቲካ ነክ የሆነና የመሰላቸውን እንዲሁም ደሞዝ የሚከፍለን መንግስት ተነክቷል ብለው ያሰቡትን በግልፅ ይቆርጡታል፡፡ ይህን ካልቆረጣችሁ “እኛ በህይወት እያለን አይታይም” ይላሉ፡፡ እኛም በ“ታስጨርሽኛለሽ 2” የገጠመን ይሄው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የአርቲስት ጌትነት እንየው “ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘ ቴአትር መድረክ ላይ ለእይታ ከበቃ በኋላ የመታገድ እጣ ገጥሞታል፡፡ ሌሎች እንዳንተ የታገዱ ፊልሞችን ታስታውሳለህ?
ትከክል ነው፡፡ የጌትነትም “ወይ አዲስ አበባ” መድረክ ላይ ለእይታ ከቀረበ በኋላ ነው የታገደው፡፡ እኔ በጣም የማዝነው፣ በአገራችን ሳንሱር ያለው ተውኔትና ፊልም ላይ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ለምን ብለሽ እንደ ጓደኛ ቀረብ ብለሽ ኃላፊዎችን ስትጠይቂያቸው፤ “አይ ግጭት፣ ረብሻና ብጥብጥ ወይም አብዮት ያስነሳሉ ብለን ስለምንሰጋ ነው” ይሉሻል፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ታሪክ፤ የተነሱ አብዮቶች፤ በፊልምና በቴአትር ሳይሆን በሙዚቃ ነው፡፡ 

የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከት፤ ወደ ኦሮሚያ ስትሄጂ እንደ እነ ሀቃሉ ያሉ ወጣቶች የዘፈኑት፣ በሌላም አካባቢ ያሉት በዘፈናቸው አብዮት መቀስቀስ ችለዋል፡፡ ግን ሙዚቃ ሳንሱር አይደረግም። በግጥም ሰው ይነቃቃል፤ ኮንሰርት፣ የቲቪ ድራማዎች … እነዚህ ሁሉ ሳንሱር አይደረጉም፡፡ እርግጠና ሆኜ የምነግርሽ፤ለዚህ የፊልም ሳንሱር መነሳት ዋነኛው ምክንያት እኛ ነን፡፡  

እነ “ግንቦት ሰባት”፣ እነ “ኦነግ”፣ እነ “ኢሳት”-- ይቅርታ ተደርጎ ወደ አገር እየገቡ፣ ስለ መደመር፣ ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር በሚዘመርበት በዚህ ወቅት፣ የእኛ ዘርፍ ለምንድን ነው ታንቆ የቀረው? በሚል ኮሚቴ አቋቁመን፣ የፊልም ስራዎች ማህበርን አስተባብረን፣ ጋዜጠኞችን ጨምረን ሄደን በመሞገታችን፣ ይሄው በረከቱ ከእኛ ፊልም አልፎ፣ ለሁሉም ፊልም ሰሪዎች ተረፈ፡፡ 

ይሄ ስርዓት አንዱን አቃፊ፣ ሌላውን ገፊ መሆን የለበትም በሚል በግልፅ ተቃውመናል፤ ተሟግተናል፡፡ ይሄንን በፊት ለነበሩት ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆን አሁን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ የቢሮው ኃላፊ ሆኖ ከተሾመም በኋላ፣ ሳናርፍ ሄደን ተሟግተን ነው፣ ይሄን ውጤት ያመጣነው፡፡ በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ከአንተ ውጭ ይህን የፊልም ሳንሱር ለማስነሳት የፊልም ሰሪዎች ማህበር፣ የፕሮዲዩሰሮች ማህበርና ሌላው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት --- ምን ያህል ርቀት ተጉዘዋል ትላለህ?
በጣም የምናደደውና የማዝነውም … በነዚህ የዘርፉ ሰዎች ነው፤ ተባብረን አብረን ብንጮህና ብንታገል ኖሮ፣ የፊልም ሳንሱር ዛሬ ሳይሆን ድሮ ይነሳ ነበር፡፡ እንደውም የኢትዮጵያን የፊልም ፖሊሲ እየተመለከትኩት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፊልሞች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሳንሱር እንዳለባቸው ይደነግጋል። 

ይሄ ፖሊሲ ሲቀረፅና ለውይይት ቀርቦ ሲፀድቅ፣ አብረው ቁጭ ብለው ተስማምተው ያፀደቁ የፊልም ባለሙያዎች ማህበር አባላት፣ የማህበር አመራሮችና ለፊልም ተቆርቋሪ ነን ባዮች … ሳንሱር በፖሊሲ ደረጃ ሲፀድቅ ራሳቸው፣ አጨብጭበው አጸድቀዋል፡፡ ይሄ በጣም አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ካስፈለገም ይቻላል፡፡

ቀጥሎ ደግሞ በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን ሳንሱር ለማስነሳትና ከፖሊሲው እንዲወጣ ክርክራችንን እንቀጥላለን፡፡ እንደ ማህበር፤ የአንድ ሰው ፊልም ሲታገድ፣ እንደ መታገል፣ የዚህ ፊልም ጉዳይ የእከሌ ነው፡፡ የ“ታስጨርሽኛለሽ” ጉዳይ የሀብታሙ ብቻ ነው ብሎ በቸልታ ማየት፣ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ 

እንደኔ ፊልም የመታገድ ገፈት የቀመሰ ፊልም አለ ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን በስም ባላስታውሳቸውም፣ በርካታ ፊልሞች ከተሰሩ በኋላ ስንት ጊዜ፣ ጉልበት፣ እውቀትና ገንዘብ ከፈሰሰ በኋላ ግምገማ ላይ ሲቀርቡ “ይህን ቁረጥ፣ ይህን አውጣ፣ ይህን አስወግድ” ይሏቸዋል፡፡ ለገምጋሚዎቹ ቀላል ነው፣ ምንም አይመስላቸውም፡፡  

ገምጋሚ ነን ባዮቹ፣ ያልገባቸው ግን፣ አንድ ትዕይንት ለመስራት ከ10 እስከ 15 ቀን ልትደክሚ ትችያለሽ፡፡ ከ200ሺህ ብር በላይ ልታወጪ ትችያለሽ፡፡ በጣም ብዙ የሰው ጉልበት፣ የጊዜ፣ የሞራልና የገንዘብ ኪሳራ ውስጥ መግባቱ ሳያንስ፣ አንድ ፊልም አንድ ሲን ተቆርጦ ሲወጣበት፣ ጠቅላላ የፊልሙ ሀሳብና ሁሉ ነገር አፈር ድሜ ይበላል። ታዲያ እነሱ ይሄንን ሁሉ የት ያውቁታል፡፡

ግን እኮ “ታስጨርሽኛለሽ 2” መታየት ጀምሮ ነበር … አይደለም እንዴ?
አዎ መታየት ጀምሮ ነበር፤ ቆመ እንጂ፡፡ ምን መሰለሽ---መጀመሪያ ላይ ትንሽ ነገር እንድንቆርጥ ተደርጎ ነበር፡፡ ለምሳሌ ስለ “ግንቦት ሰባት” የምናወራበት ላይ ስለእነ ብርቱካን ሚደቅሳና ስለ 97 ምርጫ የምንገልፅበት ቦታ ላይ፣ “የእኛን ጠላቶች ታሞግሳላችሁ” ብለው፣ የደበራቸውን ቦታ አስቆርጠውን ነበር፡፡ 

እኛ የተቆረጠውን አሳይተን ከግምገማ ስንወጣ፣ “በፍፁም የተቆረጠውን ፊልም ለእይታ አናቀርብም” የሚል ስምምነት ላይ ደረስን። እነሱ በጉልበት እንጂ ህገ መንግስቱ ይህን አይልም። ፊልሙ ተመልካች ጋ መድረስ ያለበት ከእነ ሙሉ መልዕክቱ ነው፡፡ መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት መክፈል አለብን ብለን፣ የቆረጥነውን ነገር እንደገና አስገብተን ማሳየት ጀምረን ነበር፡፡

ከዚያስ?
ከዚያ በኋላ የሚገርምሽ---የተከሰስነው በእሱ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ ሹመኞች፤ “እኛን ለመንካት ነው” በሚል የተለያየ ትርጉም መስጠት ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ፊልሙ ላይ ውሻ ነበረ፡፡ ውሻው፤ ሴትየዋ ለምርጫ ቅስቀሳ ስትወጣ ይነክሳትና ምርጫው ይስተጓጎላል፡፡ “ውሻው ምርጫውን ለማስተጓጎል ሆን ብሎ ነው የነከሰኝ” ትላለች - ሴትየዋ። ይሄ ዲያሎግ አለ - ፊልሙ ላይ፡፡ “ውሻው ማነው? እኛን ነው ውሻ ለማለት የፈለጋችሁት” አሉ፡፡

እውነት ውሻው ማን ነው? ምንን ለመወከል ነው የሞከራችሁት?
አቦ ተያ! እዚህ ላይ አንድ የሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ ግጥም ይመጣብኛል፡፡

“ስለወንበር ስንፅፍ ስልጣን ነው እያሉ፤

ስለመንገድ ስንፅፍ ስደት ነው እያሉ

ስለመሳው ስንፅፍ ምፀት ነው እያሉ

አስበን ያልነውን አስበው ሳይሰሙ

እኛን አሳደዱ እኛን አሰቀሉ፡፡” 

ይላል፡፡ በነገራችን ላይ የፈለጉትን ትርጉም መስጠት ይችላሉ፡፡ የኪነ ጥበብ ሙያ የፈለግሽውን ትርጉም ለመስጠት ምቹ ነው፡፡ ያ የተርጓሚውን የመረዳት ልክ ያሳይሻል፡፡ ነገር ግን ደራሲው በዚያ መጠን ተመልክቷል፣ ዳይሬክተሩ ይህንን ለማለት ፈልጎ ነው የሰራው … ብሎ መደምደም ግን ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ አንቺ አንድ ወንበር ይዘሽ ብትሄጂ፣ ወንበሩን 50 ዓይነት ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ገምጋሚዎቹም ጫናና ፈተና ስለነበረባቸው፣ በቀላሉ የሚያልፉት ጉዳይ አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሌም የሚያሳዝነኝ አንድ ነገር አለ፡፡

ምንድን ነው?
ይሄ ፊልም በታገደ ማግስት፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ሰራተኛ የነበሩ ግለሰቦች … ገምግመው የማሳያ ፈቃድ የሰጡን ሰዎች ማለት ነው፡- አቶ ሰለሞንና ወ/ሮ አዳነች-- ባልሳሳት … ስሟ እንደዛ ነው … ቀጥታ ከስራ ተባረሩ፡፡ “እናንተ ከሰዳቢዎቻችንና ከጠላቶቻችን ወገን ናችሁ” ተብለው፣ በወቅቱ የቢሮው ኃላፊ በነበሩት አቶ ገብረፃዲቅ በተፃፈ ደብዳቤ ተባረሩ። ልጅቷ ስትባረር በጣም የሚያሳዝነው፣ ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ 

ትንሽ እግሯንም ያማት ነበር፡፡ አቶ ሰለሞንም የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው፤ ቤተሰቦቻቸውንና ልጆቻቸውን ለአደጋ ጥለው፣ ለችግርና ለሞራል ውድቀት ተዳርገው ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት ያለ ስራና ያለ ደሞዝ በስቃይ አሳለፉ … ተመልከቺ የሚሰራውን ግፍ፡፡ ፊልሙ በታገደ ሰሞን፤ እኛም ላይ ይደርስብን የነበረው ማሸማቀቅ፣ ጉሽሚያ፣ የሞራል መንካት ጉዳዮች-- ያመን ነበር፡፡  

እነዚህ ግለሰቦች ለአንድ ዓመት ያለ ደሞዝ ተሰቃይተው፣ በፍርድ ቤት ተሟግተውና ተከራክረው ወደ ስራቸው ተመለሱ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጀግንነት፤ መሳሪያ ታጥቆ፣ ግፍን ከሚዋጋ ጀግና ወታደር የሚያንሰው በምንድነው? በዚህ አጋጣሚ ስለ ጀግንነታቸው፣ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመዋጋት ለከፈሉት መስዋዕትነት፤ በራሴና በፊልሙ ማህበረሰብ ስም ያለኝን አክብሮት ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡

እንግዲህ በፊልም ላይ የተጣለው ሳንሱር ተነስቷል። ተነስቷል ሲባል መቶ በመቶ ነው ወይስ--?
ጥሩ! እኔ የተከለከለ ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም፡፡ የተፈቀደ ነገር ሁሉ ትክክል ነው ለማለት አይዳዳኝም። እኔ በግሌ፤ ሳንሱር ተነሳ ሲባል እንደ ባለሙያ የበለጠ ኃላፊነት እንደተጣለብኝ ነው የምቆጥረው፡፡ ተናገር ስለተባልኩ ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ እውቅና ለማጋበስ፣ ለህዝብና ለአገር የማይጠቅም፣ ከፋፋይና እርስ በእርስ የሚያባላ ሀሳብ እፅፋለሁ ማለት አይደለም።  

ይበልጥ ኃላፊነት፣ ይበልጥ ጥንቃቄ እንዳደርግ ኃላፊነት የሚጭን ነው፤ ስለዚህ የተሰጠኝን ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በቀጣይ ነፃ በሆነ መንፈስ፣ ለአገር ለማህበረሰብ የሚጠቅም፣ የሚያዝናና እና የሚያስተምር ስራ እሰራለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

በመጨረሻም ከእስር የተፈታው ፊልማችን፣ ከጥቅምት 23 ጀምሮ ለእይታ ይቀርባል፡፡ በአገር ውስጥ በክልልና በውጭ - በካናዳና በአሜሪካ እንዲታይ፣ ኔትዎርክ እየዘረጋንና እየተነጋገርን ነው፡፡ ምርቃቱ ህዳር መጀመሪያ ላይ ወይ ሂልተን ካልሆነም በብሔራዊ ቴአትር ይከናወናል፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ ሳንሱሩ እንዲነሳና ፊልማችን እንዲፈታ ከጎናችን ሆኖ ሲያግዘን ለነበረው የህግ አማካሪያችን፣ ጠበቃ ታዬ በዛብህ፤ ለቀናነቱና ለበጎነቱ እጅግ አመሰግነዋለሁ፡፡ ሌላው ከጎናችን ሆኖ፣ በሀሳብም በገንዘብም ሲያግዘን ለነበረው ወንድማችን አንዋር አህመድ ሲራጅና ለወዳጃችን ሄኖክ ተሰማ --- የከበረ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ 

እናንተ ሶስት መልካም ሰዎች፤ ብድሩን ፈጣሪ ይክፈላችሁ እላለሁ። በተለይ እንደ እናቴ ልጅ የማየው አንዋር አህመድ ሲራጅ፤ በድካሜም በደስታዬም አብሮኝ ነበር፡፡ የተለየ ምስጋና ይድረሰው እላለሁ፡፡ 
አመሰግናለሁ፡፡


Post a Comment

0 Comments