ያረጁ አቁማዳዎች እየፈነዱ ነው! ከወንድወሰን ተሾመ



ያረጁ አቁማዳዎች እየፈነዱ ነው! ከወንድወሰን ተሾመ

ጁሊየስ ቄሳር ጠንካራና ደፋር መሪ ነበር፡፡ አንዳንዶች በቆራጥነቱ፣ በድል አድራጊነቱና በድፍረቱ ሲደሰቱበት ሌሎች ደግሞ በጠንካራ እርምጃዎቹ ይፈሩትና ይከፉበት ነበር፡፡ ጁሊየስ ቄሳር፤ ብሩተስ (Brutus) የተባለ ወዳጅ ነበረው፡፡ ብሩተስን ያምነው ነበር፤ ብሩተስን እንደ ጓደኛ ተቀብሎት ነበር የኖረው።  


የጁሊየስ ቄሳር ሌሎች ወዳጆች፣ ከፊት ለፊቱ ባለው የሴኔት ስብሰባ፣ በሴኔት ሰዎች በኩል፣ በእሱ ላይ የተቀነባበረ ደባ እንዳለ በመንገር አስጠነቀቁት፤ ሚስቱም እንባዋን እያዘራች ወደ ሴኔቱ ስብሰባ እንዳይሄድና ከቤት እንዳይወጣ ተማፀነችው፡፡ ወደ ሃያ የሚሆኑ ጦርነቶችን በድል የተወጣው ደፋሩ ሰው ግን ማንንም አልሰማም፤ በእሱ ያልተደሰቱና ተስፋ የቆረጡ ሴናተሮችን ደባ አልፈራም፤ እናም ቀጥ ብሎ ወደ ሴኔቱ ስብሰባ አዳራሽ ገባ፡፡ 

በከፍተኛ ፈገግታ ወደ አዳራሹ የገባውን ጁሊየስ ቄሳርን አንድ ሴናተር ያነጋግረው ጀመር፣ ወዲያውኑ በዚህ ታላቅ ሰው ዙሪያ እንደ ወትሮው ሌሎች ሰዎች ተሰባስበው፣ ንግግሮቹን መስማት ጀመሩ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሰዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ጀግናውን ለማድነቅና በፊቱ ሞገስ ለማግኘት ሳይሆን ደባ ሸርበው፣ በወገቦቻቸው ላይ ቢላና ጩቤ ይዘው የተገኙ ናቸው፡፡  

ካስካ (Casca) የተባለው የድሮ ጠላቱ፣ ጩቤውን አውጥቶ፣ በጀግናው ጁሊየስ ቄሳር ላይ ሰካበት፡፡ ጁሊየስ ቄሳር ራሱን ለመከላከል ሲሞክር እጁን የሚጠመዝዙና ስለት የሚመዙ ሰዎች በሱ ላይ መረባረብ ጀመሩ፡፡ ጁሊየስ ቄሳር ቀና ሲል የቀድሞ ወዳጁን ብሩተስን ተመለከተው፤ ያልጠበቀው ሰው ከገዳዮቹ መካከል ተገኝቷል፣ በጣር ውስጥ ሆኖ ሁለት ቃላት ተናገረ፡- “---ብሩተስ አንተም?” ነበር ያለው፡፡ ብሩተስ ያረጀ አቁማዳ ነው! ፍቅር፣ ርህራሄና ሃዘኔታ የሌለው! ብሩተስ የፈነዳ አቁማዳ ነው! የጓደኝነትና የወዳጅነት እሴቶችን መሬት ላይ የጣለ - መልካምነት የጎደለው ማንነት የተላበሰ ነው! 

ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ አያኖሩም፤ ካኖሩ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፡፡ ያረጀ አቁማዳና የአዲስ የወይን ጠጅ ምሳሌ፣ በአዲስ ኪዳን ዘመን ለነበሩ ሰዎች የተነገረ ነበር፡፡ በኦሪት ህግ ፤ አይን በአይን፣ ጥርስ በጥርስ ወዘተ በሚለው ትምህርት የኖሩ ሰዎች፤ በመለኮት አሰራር ከድንግል ማሪያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ትምህርት ይዞ ሲመጣ፣ አብዛኞቹ አዲሱን ትምህርት መቀበል ተሳናቸው።  

አዲሱ ትምህርት ስለ ፍቅር፣ በእምነት ስለሚገኝ ፅድቅ፣ ስለ ይቅርታና ተስፋ ወዘተ እሴቶች ነበር፡፡ ለዚህ ትምህርት በጎ ምላሽ መስጠት ለተቸገሩ ሰዎችና በቀደመው የኦሪት ህግ መቀጠል ለፈለጉ ፃፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ምሳሌ ተናገረ፤ “በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈሳል--” አላቸው፡፡ 

አቁማዳ ከከብት ወይም ከፍየል ቆዳ የሚሰራ ወይን ጠጅ መያዣ ነው፡፡ አቁማዳ አዲሱን የወይን ጠጅ እንዲይዝ ሁለት ነገር ማድረግ ያስፈልጋል፤ አቁማዳው አርጅቶ ከሆነ አቁማዳውን በዘይት ማለስለስ አለያም አዲስ አቁማዳ መጠቀም፡፡ መልእክቱ የደረሳቸው ሰዎች (አቁማዳዎች) አዲሱን የወይን ጠጅ (አዲሱን ትምህርት) እንዲቀበሉ ከተፈለገ፣ የሁለት ወገን ድርሻና ሃላፊነት አስፈላጊ ነው፡፡

1ኛ፡- የወይን ጠጁን የሚጨምረው ሰው መጀመሪያ አቁማዳዎቹ (ያልተለወጡ ማንነቶች) ማርጀታቸውን አስተውሎ፣ አቁማዳዎቹን በዘይት ማለስለስ (አመለካከታቸውን መቀየር) ይጠበቅበታል። ትምህርቱን በሂደት እንዲማሩ በማድረግ ያስተካክላቸዋል፡፡ አሊያ ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአረጀ አቁማዳ መጨመር የወይን ጠጁን ማባከን ያመጣል፤ በተጨማሪም የወይን ጠጁን የሚጨምረውንም ሰው ትዝብት ላይ ይጥለዋል - ወይን ጠጁን ምን ውስጥ ነው እየጨመረው ያለው? የሚል ትዝብት!

2ኛ፡- ይሄ ጉዳይ የወይን ጠጁን የሚጨምረው ሰው ሃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ በሰው ሲሆን ነገሩ ቀላል አይደለም- ያረጀ አቁማዳውን ወስደህ ዘይት ውስጥ አትነክረውም፡፡ ምሳሌው የተነገረላቸው አቁማዳዎች ለመታደስ ፈቃዳቸውን መስጠት ይጠበቅባቸዋል - ሰዎች ናቸውና፡፡  

ስለዚህ የወይን ጠጁ መፍሰስ በሁለቱም ወገን በሚፈጠር ክፍተት ሊመጣ ይችላል፡፡ በየትኛውም ምክንያት እነዚህ ያረጁ አቁማዳዎች ካልታደሱ አዲሱን የወይን ጠጅ መሬት ላይ ያፈሱታል፤ ስለዚህም ጥቅም ላይ ሳይውል ይቀራል፡፡ በነገራችን ላይ ለምን ያረጁ አቁማዳዎች ለመታደስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ? ምክንያቱ ለውጥን መፍራታቸው ነው! ለውጡ በእነሱ ጥቅም አለያም ቆምንለት በሚሉት ዓላማ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያመጣል የሚል ስጋት ስላላቸው ነው። በሌላ በኩል፤ ያረጀው አቁማዳ መታደስ ካልፈለገ፣ ወይን ጠጁን የያዘው አካል አዲስ አቁማዳ ውስጥ ይጨምረዋል፡፡ 

ይህም የተለወጠ ማንነት (አዲስ አቁማዳ) ባላቸው ሰዎች ላይ አዲስ የወይን ጠጅ (አዲስ ትምህርት) መጨመር፣ የወይን ጠጁን በወጉ ይዘው ለብዙ ሰዎች ጣዕም ያለው መጠጥ እንዲሰጡ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አዲሱ ትምህርት ለኔ፣ ለቤተሰቤ፣ ለማህበረሰቤና ለአገሬ ምን ይጠቅማል? ትምህርቱ ዘላቂ በሆነ መልኩ በአገራችን ሠላም ያመጣል ወይ? ብሎ ራስን መጠየቅና ለመታደስ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡  

ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ አዲስ ትምህርትና ፍልስፍና፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ናኝቷል፡፡ ይህም የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ትምህርት ነው - ይህ ማለት አዲሱ የወይን ጠጅ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ደግሞ እጅግ ብዙ ሰው ብሔርን መሰረት ባደረገ አክራሪ አስተሳሰብ፣ ‘የኛ’ እና ‘የእነሱ’ በሚል ከፋፋይ ሃሳብ፣ በበቀልና በጥላቻ ስሜት በተገነባ ማንነት (ያረጀ አቁማዳ) ኖሯል፡፡ ይህ ማንነት አዲሱን ትምህርት መቀበል አቅቶታል፡፡ በመሆኑም ያረጀው አቁማዳ መፈንዳት ጀምሯል፡፡ 

መፈናቀል፣ ሰቆቃና ስደት የኢትዮጵያውያን መለያ ሆኖ ለዓመታት በኖረበት ምድር፣ ይባስ ብሎ በዚህ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማምጣት አቅም ባለው አዲስ የመደመር፣ የፍቅርና የይቅርታ ፍልስፍና ብስራት ማግስት፣ አዲሱን ትምህርት መሸከም ያቃታቸው ያረጁ አቁማዳዎች እየፈነዱ ይገኛሉ፡፡ አቁማዳዎች ሲፈነዱ አዲሱን የወይን ጠጅ ከንቱ ከማድረጋቸውም በላይ አካባቢያቸውን ያበላሻሉ፡፡  

ያረጁ አቁማዳዎች እነማን ናቸው? ያረጁ አቁማዳዎችን በሶስት ልንከፍላቸው እንችላለን። የመጀመሪያዎቹ ያረጁ አቁማዳዎች፤ ህዝብን እርስ በእርስ የሚያጫርሱ ዘረኛ አስተሳሰቦችን የተሞሉ፣ ምንም ውስጥ በሌሉ ሰዎች ላይ አደጋ የሚያደርሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ያረጁ አቁማዳዎች፤ በአሮጌው አስተሳሰብ ተይዘው በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ መንገዶች ዘረኝነትና ጥላቻን የሚያራግቡ፣ በየቤቱና በህዝብ ውስጥ የመሸጉ ሰዎች ናቸው፡፡

ሶስተኛዎቹ ያረጁ አቁማዳዎች ደግሞ አዲሱን አስተሳሰብ ለማራመድ አቅምና ፍላጎት የጎደላቸው ተቋማት፣ መዋቅሮችና አሰራሮች ናቸው። አዲሱን ትምህርት አጠናክሮ ለመቀጠል እነዚህ ሶስት አይነት ያረጁ አቁማዳዎች ሊታደሱ አለያም ሃላፊነትና ስልጣን ካላቸው ደግሞ በአዲስ አቁማዳዎች ሊተኩ ያስፈልጋል፡፡ ሲተኩ ግን መርህን በተላበሰና ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ መሆን አለበት። ይህ እንግዲህ የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጠን፣ የለውጥ አራማጆች ሚና ሊሆን ይገባል፡፡  

ያረጁ አቁማዳዎች ፍቅርን፣ ምህረትን፣ ይቅርታን፣ ተስፋን፣ እኩልነትን፣ ፍትህን፣ ዲሞክራሲን፣ አንድነትን ይቃወማሉ፡፡ የታደሱ አለያም አዲስ አቁማዳዎች እነዚህን እሴቶች ያስተናግዳሉ፡፡ በመታደስ ላይ የምንገኝም ብንሆን አንዳንዴ ያረጁ አቁማዳ ባህርያት ብቅ ሊሉብን ይችላሉ፡፡ ተሰርቶ ያለቀ ሰው የለም፡፡ ሁልጊዜ ግን እንደ አገር በአንድነት የምንቀጥልበትን፣ በእኩልነትና በፍትህ ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና የምንጓዝበትን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከድህነት የምንወጣበትን እሴት የራሳችን ለማድረግ መትጋት ይኖርብናል፡፡ 

የጋሞ ሽማግሌዎች እሳትን በእሳት አልመለሱም፤ በቀልን በበቀል አልመከቱም፤ ይቅርታ፣ ምህረትና መደመር የሚሉት እሴቶች በጥልቀት ገብቷቸዋል። በብዙ ጉዳትና ሃዘን ውስጥ ሳሉ፤ እህት ወንድሞቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በሞትና በጉዳት አጥተው በተሰበሩበት ወቅት፣ በተግባር ይቅርታን ያሳዩን፣ ፍቅርንና መደመርን ያመላከቱን በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ሁሌም ሲከበሩና ሲታወሱ ይኖራሉ!! በዚህ ድርጊታቸው፣ ብዙ ቤተሰቦችንና ተቋማትን ማትረፋቸው የሚደነቅ ነው፡፡  

አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት መንግስት፣ የለውጥ መሪዎችና ደጋፊዎች፣ መልካም ድርጊትና አሰራርን በማስፈን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የተጀመረው ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል፣ አስተማማኝ የህግ የበላይነት ሊረጋገጥም ይገባል፡፡ 

ለእኔ፣ ከእኔ በእኔ የሚሉ የግለኝነትና የራስ ወዳድነት አስተሳሰቦችን አስወግደን፣ እንደ አገር ልጆች ለእኛ፣ በእኛ ከእኛ የሚሉ እሴቶችን በመያዝ ሰብእናችንን እናድስ! እያንዳንዳችን በየዕለቱ በአዕምሯችን በመታደስ እንለወጥ፡፡ ያን ጊዜ አዲሱን የወይን ጠጅ የሚይዝ አዲስ አቁማዳ እንሆናለን፡፡ ያን ጊዜ “ብሩተስ አንተም?” የምንለው ሰው አይኖረንም! ቸር እንሰንብት!!

*** ወንድወሰን ተሾመ የማህበራዊ ሳይንስና የሥነ ልቦና ባለሙያ
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- wondwossenteshome@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡



Post a Comment

0 Comments