በአሜሪካ ቀይመስቀል በኩል ወደ ኬንያ ለስደተኞች የሚላከውን ገንዘብ ትላንት ለአሜሪካ ቀይ መስቀል ያበረከቱት የትብብሩ ሰብሳቢ አቶ ታማኝ በየነና ሌሎች የትብብሩ አመራሮች መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
መጋቢት 1 ቀን 2010 በመከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ወደ ኬንያ የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን በሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ጭምር ማረጋገጫ መስጠቱ ይታወሳል።
እነዚህን ዜጎች ለመታደግ አለም አቀፉ ቀይ መስቀል እየተንቀሳቀሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያንም ለወገኖቻቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን የአሜሪካ ቀይ መስቀል ሃላፊዎች አመስግነዋል።
ግሎባል አሊያንስን በመወከል ለተፈናቃዮቹ በአሜሪካ ቀይ መስቀል በኩል የአስር ሺ ዶላር ስጦታውን ያበረከተው አክቲቪስት ታማኝ በየነ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ግሎባል አሊያንስ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች በቅረቡ የ25ሺ የአሜሪካን ዶላር በኦሮሞ አባገዳዎች በኩል መላኩም ይታወሳል።
በወልዲያ በተፈጸመው የመንግስት ሃይሎች ግድያ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና የመቁሰል አደጋ ለደረሰባቸው 21 ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የ10ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉንም መረዳት ተችሏል።
በቅርቡ ከእስር ለተፈቱና ወደ ክልላቸው ለመሄድ የትራንስፖርት ችግር ለገጠማቸውና መሰል ችግር ላለባቸው 33 ተፈቺዎች ለእያንዳንዳቸው 10ሺ ብር በተመሳሳይ መለገሱም ታውቋል።
0 Comments