ሁልግዜም የማይሆን የሚሆንባት አገር! መስቀሉ አየለ

የሩቁን ትተን ከቅርብ እንነሳ – ከሸዋ ተማርኮ መቅደላ እስር ቤት ዘብጥያ የወረደው ብላቴናው ሚኒሊክ ከእስር አምልጦ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮትዮጵያ ለመሆን መብቃቱ የታሪክ እንቆቅልሽ ነው።




መቶ አመት ከፈጀው የዘመነ መሳፍንት ጦርነት ያላገገመችው አገራችን ጣሊያንን በአድዋ ላይ ትመታለች ብሎ ማን ሊያስብ ይችል ነበር?

አጼ ሚኒልክን ያህል ብልህና አስተዋይ ዙፋናቸውን ለእያሱ ማውረስ ይሳናቸዋል ብሎ ማን ያምን ነበር?

በብዙ የውስጥ መጠላለፍ ወደ ከፍታው የመጡት ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ አርባ አመት በነገሱባት ኢትዮጵያ መፍጠር የቻሉትን አለማቀፋዊ ተጽእኖ ላየ ሰው እዚህ ግባ በማይባሉ ጥቂት አስር አለቆች ተጠፍንገው ሽንት ቤት ውስጥ ይቀበራሉ ብሎ ማን ያስባል?

አገሪቱ ወደ ሰለጠነው አለም ጎረራ እቀላቀልበታለሁ ብላ ለመጀመሪያ ግዜ ዘመናዊ ትምህርት ያስተማረችው የፊደል ሰራዊት
  1. ታሪክ ብሎ ነገር የለም፤ የሰው ልጅ ታሪክ የመደብ ትግል ነው፤
  2. ንጉስ ብሎ ነገር የለም፤ አድሃሪ እንጅ።
  3. የራስ ሃገር ብሎ ነገር የለም፤ አለም የወዛደሮች ናት፤
  4. እግዚ አብሔር የለም(ሎቱ ስብሃት)፣ ለሞት ፍርሃት መሸሻ ሲባል በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ ኮንስትራክትድ የሆነ ኢሜጅ ነው ወዘተ በሚል ጉሽ ጠላ ሲሰክርና ማንነቱ የቆመበትን ምሰሶ (ፒላር) ሁሉ አውልቆ ከምስራቅ አገሮች በተነሳ የክህደት ማእበል ሲናጥማእ ሲናጥ ኢህአፓ ከዚያም መኢሶን ብቻ ነበሩ። እንግዲህ አለማቀፋዊ ነን የሚሉት የያኔዎቹ አውራ ጀብደኞች ማንነታችንን ሁሉ ተረት ለማድረግ እንደሞከሩት ተረት ይሆናሉ; ትግሉም እንዲህ ወደ ጎሰኞች መንደር ይወርዳል ብሎ ማን ሊያምን ይችላል?
ከህልቁ መሳፍርት መበላላት ቦሃላ ብቻውን ገኖ የወጣው መንግስቱ የተባለ ጎረምሳ ወታደር በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው ግዙፍ ጦር የሚገነባና የሚፈራ መሪ ሆኖ ይወጣዋል ብሎ ማን ያምን ነበር?

ጥቂት መደዴዎች አህያ እየነዱ ቤተመንግስቱን ይገቡበታል፤ ያም ግዙፍ ጦር እንደ ጥሬ ቆሎ ሜዳ ላይ ተበትኖ መሪዎቹም ከነቦርጫቸው ዘብጥያ ወርደው በጭንቅላታቸው የእንጀራ ሞሰብ ሳይቀር ተሸክመው የሚያመላልሱበት ዘመን ይመጣል ብሎ ማን ያስብ ነበር?

ወያኔን በአንቀልባ አዝሎ አዲስ አበባ ያስገባው ሻቢያ በወያኔ ትክዶ እንዲህ ውራ ይወጣል ብሎ ማን ያስባል?

መለስን፣ አቡነ ጳውሎስንና አላìሙዲንን የያዘው ባለ ሶስት እራሱ እባብ ጭንቅላቱ ተቆርጦ እንዲህ ጅራቱ ብቻ ይንከላወሳል ብሎ ማን ይገምታል?

ክንደ ብርቱው አንዳርጋቸው ጽጌ እንደ ውሻ ትውከት በሚንቃቸው ሰዎች እጅ የገባብትን ሂደት ማን ቀድሞ ሊያሰላው ይችላል?

ቁጥሩ ቀላል የማይባል የኢትዮጵያ ህዝብ መለስ ዜናዊ ወደ ገሃነም ሲወርድ ዳንኪራ የመታውን ያህል ለኢሳያስ አፈወርቅ ጤና የሚጸልይበትን ዘመን አይቶ ማመን ይቻላልን?

ወያኔ በመልኩ ጠፍጥፎ የሰራው ኦህዴድ እንዲህ የወያኔ እግር እሳት ይሆናል የሚል ራእይ ይኖረን ዘንድ ከነቢያት ልጆች እነማንን መሆን ነበረብን?

“ከዚህ ቦሃላ ነኪ የለንም” እያለ ሲደነፋ የኖረው የስርአቱ የጡት አባት ጃተኔው ስብሃት ነጋ እንዳለው “የሃይል ሚዛኑ ከእጃችን ከወጣ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይን ህዝብ ይበላል፤ቀጥሎም የትግራይ ህዝብ በፋንታው የአድዋን ህዝብ ይበላል” ሲል የተናገረውን ስጋት ከጥቂት ግዜ በፊት ማሰብ ይቻል ነበርን?

ብቻ – ያለፈው ታሪካችን እንደሚያሳየን የዚህችን አገር እጣ ፋንታ በራሱ መንገድ ገፍቶ ጫፍ ያደረሰ ማንም የለም።ታሪካችንን የቻልነውን ያህል እጅግ ወደኋላ ብንገፋውም ሂደቱ ይኼው ነው። ኢትዮጵያ ማለት ሁልግዜም የማይሆን የሚሆንባት አገር ናት!

Post a Comment

0 Comments