ህወሀቶች ተሰልፈው ገብተው ነበር። ነባሮቹ አመራሮች፡ ያለቦታቸው፡ ያለስልጣናቸው ተያይዘው የገቡበት የሞት ሽረት ያህል የተወስደው ስብሰባ መጨረሻው ለህወሀቶች መልካም ዜና አላመጣም። ለሁለት ቀናት የታሰበው ሁለት ሳምንት ወስዷል። መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ጫፍና ጫፍ የረገጡ ተቃራኒ አቋሞች የተንጸባረቁበት እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም በኦህዴድና በህወሀት መሀል መስመር የለየ ፍጥጫ ተከስቷል።
በረከት ስምዖን የህወሀቶችን ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር የሄደበት ርቀት እነገዱ አንዳርጋቸው ሰልፋቸውን ይበልጥ ከለማ ኦህዴድ ጋር እንዲያደርጉ ምክንያት እንደሆናቸውም ከብአዴን አከባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በረከት የያዘው መስመር ህወሀትን ዋጋ አስከፍሏል። ህወሀትን ለማዳን ወይም የህወሀት ሎሌ የሆነ ሊቀመንበር እንዲመረጥ በበረከት በኩል የነበረው ሩጫ ድምሩ ዜሮ ሆኖ ቀርቷል። ህወሀት ደጋፊ እንዲያጣ በማድረግ በመጨረሻም ህወሀት ባልፈለገው ውጤት ስብሰባው እንዲጠናቀቅ አድርጎታልም ይባላል። ድሮም በረከትን ውሽማውን እንደቀማው ደመኛ የሚጠላው ስብሃት ነጋ ይሄኔ የበረከትን ጭንቅላት በሽጉጥ ቢበረቅሰው የሚፈልግ ይመስላል። ገደል ይዞአቸው ገብቷልናል።
የሊቀመንበር ድምጽ አሰጣጡ ከመከናወኑ በፊት በቀረቡት እጩዎች ላይ የተደረገው ክርክር አስገራሚ ነበር። በተለይ ህወሀቶች ዶ/ር አብይ ላይ የውሸት ዶሴ ከፍተው ስሙን በሚያጎድፉ ውንጀላዎች ሲያብጠለጥሉት እንደነበር ውስጥ ከነበረ አንድ ሰው የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ሌላው ቀርቶ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ አሟሟት የዶ/ር አብይ እጅ አለበት የሚል ክስ በህወሀቶች ተነስቶ እንደነበርም ተሰምቷል።
ህዝበኝነት፡ ከድርጅት መስመር ማፈንገጥ፡ በግል ተወዳጅነት የሰከረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መጠመድ የሚሉ ስድብ ቀረሽ ውርጅብኝ ከህወሀቶች በየተራ ሲጎርፍም ነበር ተብሏል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማ ድምጽ በቀረበበት ዕለት ሆን ብሎ ጠፍቷል በሚልም ከእነበረከት ሳይቀር የውግዘት መዓት መቅረቡም ተሰምቷል። በመጨረሻው ስድስት ሰዓታት ህወሀቶች የዶ/ር አብይን መመረጥ ለማጨናገፍና ለማስቀረት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። የብአዴንና የደኢህዴንን አባላት በቡድናና በተናጠል እየተጠሩ ድምጻቸውን ለሽፈራው ሽጉጤ እንዲሰጡ በህወሀቶች በኩል የተደረገው ብርቱ ጫናና ማስፈራራት ያልተጠበቀ ውጤት ማስከተሉ አልቀረም።
ያደፈጠው ብአዴንና ያልተጠበቀው ደኢህዴንኦህዴድ ጀመረው። ደኢህዴን አጀበው። ብአዴን ዙሩን አከረረው። በመጨረሻም ኦህዴድ ገመዱን በጥሶ ገባ። ህወሀት በባዶ አጨብጭቦ ወጣ። የሰሞኑ ስብሰባ በአጭሩ ከተገለጸ ከዚህ አያልፍም። እውነት ለመናገር የሰሞኑ ስብሰባ ኮከብ ተጫዋች ብአዴን፡ ኮከብ ጎል አግቢ ደኢህዴን፡ ሻምፒዮን በመሆን ዋንጫውን የወሰደው ደግሞ ኦህዴድ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ህወሀት የጸባይ ዋንጫ እንኳን ተነፍጎት ጨዋታውን አጠናቋል።
የገዱ ብአዴን ከለማ ኦህዴድ ጋር የጀመረውና ህውሀቶችን በጥፍራቸው ያስቆመው ወዳጅነት በመሀል የቀዘቀዘ መስሎ ነበር። በሰሞኑ ስብሰባ ዳግም አንሰራርቶ ህወሀትን ጉድ ሰርቷል። ብአዴን በዶ/ር አብይ መመረጥ ላይ የተጫወተው ሚና አስገራሚ ነበር። ህወሀቶች በቀላሉ የብአዴኖችን ድምጽ ወደ ሽፈራው ሽጉጤ እናደርገዋለን የሚለው ተስፋቸው ውሃ በልቶት ቀርቷል። ድምጽ የነፈጉት የገዛ ፓርቲቸው ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ሁለት ድምጽ ብቻ ማግኘቱ የህወሀቶችን ሽንፈት ቅስም ሰባሪ ያደርገዋል።
ያደፈጠው ብአዴን ሙሉ ለሙሉ በሚያሰኝ መልኩ ድምጹን ለዶ/ር አብይ ሰጥቷል። ያልተጠበቀው ደኢህዴንም ህወሀትን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎታል።
ቀላል የማይባል የደኢህዴን ድምጽ ለዶ/ር አብይ ተደምሯል። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ያገኙት አብዛኛው ድምጽ ከደኢህዴን ይልቅ የህወሀትን ነው። ህወሀቶች ድምጻቸውን በሙሉ ለሽፈራው ቢሰጡም የሽጉጤን ልጅ ከሚኒሊክ ቤተመንግስት የሚያስገባላቸው አልሆነም። ሌላው ምርጫቸው የነበረው ደመቀ መኮንንም በምክትልነት የያዘውን ቦታ በመቀጠሉ ቀድሞውኑ ውድድሩ ውስጥ አለመግባቱ ታውቋል። እናም ህወሀቶች ከስብሰባው ሲወጡ በንዴት ጦፈው፡ ተኮራርፈው፡ እየተወራጩ እንደነበረ ከውስጥ የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ብአዴንና ደኢህዴን የያዙት አቋምና ለዶ/ር አብይ መመረጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ የህወሀቶችን የበላይነት ያፈራረሰው ይመስላል። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እያሳበቡ፡ ከመስመር ወጥታችሁ በሚል የቃላት ዱላ እየደበደቡ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በሚል አባል ድርጅቶችን እንደፈረስ ሲጋልቡ የሰነበቱት ህወሀቶች በሰሞንኛው ስብሰባ የገጠማቸው ዱብ እዳ ነበር። የኦህዴድ ማፈንገጥ እያለ ብአዴንና ደኢህዴንም ቋንቋቸውን መቀየራቸው ለህውሀት ከባድ መርዶ ነው። የመጨረሻውን መጀመሪያ በቁማቸው አዩት። ሞታቸውን አሸተቱት።
አዎን! ህወሀቶች ክፉኛ ቆስለዋል። ላለፉት 27 ዓመታት በቀጭን የስልክ መልዕክት ያሻቸውን፡ የፈለጉትን መሪ ሲመርጡ፡ ሲያስመርጡ፡ ሲሽሩ፡ ሲያባርሩ የለመዱት አሁን ጊዜ ከድቷቸው በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው የፈቀዱትን መምረጥ እንኳን ሳይችሉ ቀርተዋል። ከእንግዲህ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚቀለብሱት ውጤት አይደለም። እያቃራቸውም ቢሆን ከመቀበል ውጪ ምርጫ የላቸውም። ለኦሮሞ ተወላጅ ወንበሩን ሰጥታችሁ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጣችሁ የሚለውን የደጋፊዎቻቸውን አስፈሪ ተቃውሞ የሚመክቱበት ትከሻቸው ከዛለ መጪው ጊዜ ከባድ ይሆንባቸዋል።
በመቀሌ ከ2500 በላይ ሰዎች የሚሳትፉበት ጉባዔ የጠሩት አንድም ይህን ጉዳይ ለደጋፊዎቻቸው ሊያረዷቸውና ሊያጽናኗቸው ይሆናል። አይዟአቹሁ፡ መልሰን እናገኘዋለን ብለው በተስፋ ሊያጠግቧቸው ተዘጋጅተውም ይሆናል። ለጊዜው በህወሀቶች ሁኔታ ደጋፊዎቻቸው ግራ ተጋብተዋል። የ60ሺህ ትግራዋይ ህይወት የተገበረለትን ስልጣን አንዲት ብልቃጥ ደም ላላፈሰሱት የለማ ቡድን አባላት አስረከባችሁ የሚለው ተቃውሞ ከወዲሁ አስፈርቷቸዋል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚታየው የትግራይ ተወላጆች ቁጭት ለህወሀቶች ጥሩ ምልክት አይደለም። ከወዲሁ አዲስ የትግራይ ፓርቲ እንዲመሰረት ጥያቄ ማቅረብ ጀምረዋል።
ዶ/ር አብይ ስጋት ወይስ ተስፋ?የዶ/ር አብይ መመረጥ በነጻነትና ዲሞክራሲ ናፋቂው ጎራ በኩል የተለያዩ ስሜቶችን ፈጥሯል። ስጋታቸውን የሚያንጸባርቁ በርካቶች ናቸው። ተስፋን የሰነቁም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ከሁለቱ ሌላ ፍጹም ደስታ ያሰከራቸው፡ በአንጻሩ ደግሞ ጨለማው ብቻ የሚታያቸውም አሉ። የአንዳንድ የዲሞክራሲና የነጻነት ታጋዮችና አክቲቪስቶች በደስታ ስካር አቅል የመስታቸው ሁኔታ የሚያስፈራ ነው። ከአዲስ አባብ ኢህአዴግ የስብሰባ አዳራሽ ዜናው በጭምጭምታ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ነጻ የወጣች እስኪመስል በደስታ የተንሳፈፉ ሰዎች ሁኔታ በእርግጥም የጤና አይመስልም። መርህ የሌለው በትንሽ ድል የሚተነፍስ ታጋይ ወይም የነጻነት አቀንቃኝ ራሱን ቢፈትሽ ጥሩ ነው።
ተስፋ ማድረጉ ባልከፋ። ነገን መልካም እንዲሆን መመኘቱም ይሁን። ነገር ግን መዘንጋት የሌለብን አሁንም ከቤተመንግስት ያለው ህወሀት መሆኑን ነው። መከላከያው በእጁ ነው። ደህንነቱን የነጠቀው ሌላ አካል እስከአሁን የለም። በኢኮኖሚው ረገድ አሁንም ጡንቻው አልሟሸሸም።
የዶ/ሩን መመረጥ በጨለመው ጎኑ ብቻ የሚመለከቱትም አካሄዳቸውን ቢመረምሩት መልካም ነው። የዶ/ሩ መመረጥ በህወሀቶች የተቀነባበረና የኢትዮጵያውያንን ትግል ለመደፍለቅ የተቀመመ መርዝ ነው የሚሉት ወገኖች ህወሀትን እያጀገኑ፡ የሌለውን ጉልበት እየሰጡት፡ ሌላውን አቅም ያጣ ሁሌም ተላላኪ አድርጎ የመደምደም አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን ያወቁት አይመስለኝም ።
አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ ነጥረው ከወጡበትና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተሰሚነትን እያገኙ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ልባቸውን ጥርቅም አድርገው የዘጉት እነዚህ ወገኖች የአብይን መመረጥ ለኢትዮጵያ ከበጎነቱ ይልቅ ይበልጥ የከፋ ጊዜ ያመጣባታል ብለው በባዶ ሜዳ የሚደነብሩና ነገን የሚያጨልሙትን ፈጣሪ ይርዳችሁ ከማለት ውጪ ምን ይባላል? እነዚህ ወገኖች ማወቅ ያለባቸው ከየትኛውም ፓርቲና ግለሰብ በላይ ኢትዮጵያ ላይ ሃያል ጉልበት የሆነው የህዝብ እምቢተኝነት የለውጣችን ዋልታና ማገር፡ የነጻነታችን ምርኩዝና መሰላል መሆኑን ነው። የህወሀት ድራማ የማያንበረክከበው፡ የትኛውም ማስመሰያ ቲያትር የማያዘናጋው የማያዳክመው የህዝብ ማዕበል።
ህወሀት በእርግጥ ተዳክሟል። እንደበፊቱ ረግጦና ጨፍልቆ የመግዛት አቅም ከድቶታል። እየሰመጠ ያለ መርከብ ነው። ግን ደግሞ እንደህወሀት ያለ አገዛዝ በቀላሉ የሚላቀቁትም አይደለም። እድሉ ጠባብ ቢሆንም አፈር ልሶ አይነሳም ማለትም አይቻልም። ዘረኛ፡ ወንጀለኛ፡ ማፊያ፡ ፍጹም ጨካኝና አውሬ በሆኑ ሰዎች የሚመራ በመሆኑ ፈራርሶ፡ ወላልቆ፡ ከሩቅ ጉድጓድ ካልተቀበረ በቀር ለኢትዮጵያ ለውጥ ማሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ምንም እንኳን ህወሀት ከእንግዲህ እንደጠንካራ ድርጅት ቆሞ መሄድ የማይችል ቢሆንም እያነከሰም የእኛን ምጥ ማራዘምና ስቃያችንን መቆሚያ የሌለው በማድረግ ረገድ አቅም የሚያንሰው አይሆንም። ከእንግዲህ ህወሀት ያለልኩ ያጠለቀውን የመንግስትነት ካባ አውልቆ እልም ያለ የጥፋት ሃይል ወደ መሆን ይሸጋገራል። በተስፋ መቁረጥ ባህር ውስጥ የተነከረ በመሆኑ አጥፍቶ ከመጥፋት ውሳኔ ላይ ሊደርስ ይችላል። የዶ/ር አብይ አንዱ ፈተናም ተስፋ ከቆረጠ አረመኔ አገዛዝ ስልጣኑን በሰላም የመረከቡን እድል እንዴት ያገኛል የሚለው ነው።
በለማ ቡድን አዲስ አቅጣጫ ቀልብና ስሜቱ የተማረከ ኢትዮጵያዊ የዶ/ር አብይን መመረጥ በይሁንታ ተቀብሎታል ማለት ይቻላል። በዚህም ህዝቡ በሰፊው እየጠበቀ ነው። ዶ/ር አብይ በቃል የነገሩትን፡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ከሰቀሉት የክብር ማማ ሀገራቸውን ማየት የሚፈልጉት ኢትዮጵያውያን ከአዲሱ መሪ ቢያንስ የተወሰኑ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ከወዲሁ መጠየቅ ጀምረዋል። ለዶ/ር አብይ ትልቁና ዋናው ፈተናም ይህኛው ነው። በመጀመሪያዎቹ ቀናት ህዝቡ የሚጠብቃቸው እርምጃዎች ላይ ተመሳሳይ አቋሞች እየተንጸባረቁ ነው።
ሶስት ነገሮችን በመጥቀስ ዶ/ር አብይ ተፈጻሚ እንዲያደርጓቸው ሀሳቡን በመሰንዘር ላይ ነው። ለሁሉም የተቃዋሚ ድርጅቶች ሀገራዊ ጉባዔ እንዲጠሩ፡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ የቀሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን እንዲለቁ፡ ህዝብ ላይ የተጫነውን አስችኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሱ የሚሉት ሀሳቦች ተነቅሰው በመጀመሪያዎቹ የዶ/ር አብይ የስልጣን ቀናት ተግባራዊ እንዲደረጉ በበርካቶች ዘንድ ስምምነት ያገኙ ይመስላሉ። እንግዲህ የእኔም ሆነ የአንዳንዶች ስጋት የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው።
ህውሀት ቢዳከምም መከላከያው ውስጥ የበላይነቱ እንዳለ ነው። በደህንነቱም እንደዚያው። እነዚህን ሁለት ቁልፍ የስልጣን ማስጠበቂያ ተቋማትን እንዴት ከህወሀቶች እጅ ፈልቅቆ መውሰድ ይቻላል? እስከአሁን ምንም ምልክት የለም። እነዶ/ር አብይ ውስጥ ለውስጥ ስራ ሰርተው ከሆነ እሰየው ነው። ህወሀቶች በመከላከያና በደህንነቱ ላይ የበላይነታቸው ከተገፈፈ ጨዋታው እንደሚያበቃ ያውቁታል። ያንን በመቃብራቸው ላይ ካልሆነ በቀር የሚፈቅዱት እንደማይሆን ይታመናል፡፡ ይህ ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በእነዚህ ተቋማት ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ስለመኖሩ ፍንጭ ባልታየበት ሁኔታ የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአቶ ሃይለማርያም ይሻላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
ህወሀት አፈገፈገ ወይስ ሸሸ?አልሸሸም። አፈግፍጓል። የረባሽነት ሚና የመጫወት ስትራቴጂ መንደፉ ይጠበቃል። ከወዲሁ ለአዲሱ መሪ እሾህና አሜኬላ ከፊት ለፊቱ እየተከለ ነው። የአዲሰ አበባ ጉዳይን በእነአባዱላ ገመዳ በኩል ወደፊት በማምጣት ዶ/ር አብይ ጠረጴዛ ላይ ማኖር አንዱ የመበጥበጥ ስትራቴጂው ነው። ዶ/ር አብይን ቅርቃር ውስጥ ይከቱታል ተብለው ከሚታመኑ ጉዳዮች አንዱ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ የሚለው አጀንዳ ነው። በሚቀጥሉት ሁለት ሶስት ወራት ውስጥ የአዲስ አበባን ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከፍተኛ ጫና ለማድረግ ህወሀት ተዘጋጅቷል። ከኦሮሞ ብሄርተኞችና ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ከአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር የሚያላትመውን ይህን አጀንዳ ወደፊት በመግፋት መንገዱ ለዶ/ር አብይ አባጣ ጎርባጣ እንዲሆን በህወሀት በኩል በማፈግፈጉ ስትራቴጂ የተያዘ ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን የተፈለገ ይመስላል።
ሌላው የአብዲ ኢሌ ካርድ ነው። የሶማሌውን አጋር ፓርቲ ወደ ኢህአዴግ አባልነት ለማምጣት የተዋደቀው ህወሀት በእነለማና ገዱ የተባበረ ሃይል ከሽፎበታ። ቀጣዩ ስትራቴጂ አብዲ ኢሌን በመጠቀም የአዲሱን መሪ ስራ ማወክ ነው። ከወዲሁ በጭምጭምታ እንደሚሰማውም የህወሀት የጦር ጄነራሎች ከአብዲ ኢሌ ጋር እየመከሩ ነው። ዶ/ር አብይ የተዛባውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስተካከልና የህወሀትን ዘረፋ ለማስቆም እርምጃ የሚወስድ ከሆነ የአብዲ ኢሌ ልዩ ሃይል ጦር አከባቢውን ለማተራመስ እንዲዘጋጅ፡ ህወሀቶችም ቀውሱን ለማረጋጋት በሚል መፈንቅለ መንግስት አድርገው ዳግም ስልጣኑን መጨበጥ እንደስትራቴጂ ከኋላ ኪስ ተውሽቋል።
ህወሀት የዶ/ር አብይ ስልጣን ቀውስ የበዛበት ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት ውስጥ በመግባት በዶ/ር አብይ ላይ ፊቱን እንዲያዞር ማድረግ በማፈግፈግ ዕቅዱ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤት እንዲሆን ፈልጓል። የትግራይ ተወላጆችንም ይበልጥ በጎኑ ለማሰለፍ በአንዳንድ አከባቢዎች ትግራዋይ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲፈጸም ሊያደርግም ይችላል። ህወሀት አርፎ አይቀመጥም። ለማ እና ገዱ ድባቅ መትተው የ27 ዓመቱን መርዝ ያረከሱበትን የኦሮሞ-አማራ ጉዳይ ወደ ኋላ በመመለስ ዳግም ግጭት ለመፍጠር መፍጨርጨሩ የማይቀርም ነው። ያዳቆነ ሴይጣን ሳያቀስ መች ይለቃል?
ዶ/ር አብይ ውስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባቡር መሪ ጨብጠዋል። ፈተናው ብዙ ነው። ከያአቅጣጫው ነው። የህወሀትን አከርካሪ የሰበረው ህዝባዊ ትግሉም ተንጠልጥሏል። ዶ/ር አብይን ለመሪነት እንዲበቁ ነዳጅ የሆነው ህዝባዊ እምቢተኝነቱ መንታ መገድ ላይ ቆሟል። ይህ በጣም አደገኛ ነገር ነው። ዶ/ር አብይም ከህወሀት ጥቃት የሚተርፈው ይህ ትግል ሳይቀዘቅዝ እንደጋለ መቀጠል ከቻለ ብቻ ነው። ዶ/ሩ ሌላ ምን ጉልበት አላቸው?
በተረፈ ዶ/ር አብይ ህዝብ ተስፋ ያደረገውን ለውጥ እንዲያመጡ በግሌ እመኛለሁ። ህዝባዊ ትግሉ ግን ለአፍታም መቆም የሌለበት መሆኑን አድምቄ ለማስመር እፈልጋለሁ። አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው?……. ህዝባዊ ትግሉ አይደለምን?!!!
0 Comments