አገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዉስጥ ለረጂም ዘመን ነጻነታቸዉን ጠብቀው ከኖሩና ጥንታዊ ሥልጣኔ ካላቸዉ አገሮች ዉስጥ አንዷና ቀዳሚዋ ናት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ብሄር ብሄረሰቦች ከሚኖሩባቸዉና ህብረ ባህል ካላቸዉ አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት።
ይህ የተፈጥሮ ስጦታ አገራችን ኢትዮጵያን የተለያዩ እምነቶች የሚመለኩባት፥ ብዙ ባህሎችና ወጎች የሚገኙባትና አያሌ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር እንድትሆን አድርጓታል። ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ኢትዮጵያ ዉስጥ አዲስ አመትና የመስቀል በአላት ተከብረዋል፥ በነገዉ ዕለት ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በየአመቱ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ የሚያከብረዉ የኢሬቻ (የምስጋና በዐል) በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል።
በዚህ አጋጣሚ አርበኞች ግንቦት ሰባት በነገዉ ዕለት የኢሬቻን በዐል ለሚያከብሩ የኦሮሞ ወገኖቻችን እና ባለፈዉ ሐሙስ የመስቀል በዐል ያከበሩትን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን በሠላም አደረሳችሁ በማለት ደስታዉንና መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
አዲሱን አመትና የመስቀል በዐልን በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ በሠላም እንዳከበርን ሁሉ በነገዉ ዕለት ቢሾፍቱ ዉስጥ የሚከበረዉን የኢሬቻ በዐልም ሁላችንም ከኦሮሞ ወንድሞቻችን እና እህቶቻቸን ጋር በሠላም በማክበር የሚመሳሰሉና የሚወራረሱ አያሌ ባህሎችና የጋራ እሴቶች ያለን ህዝብ መሆናችንን ለአለም ህዝብ እናሳይ!
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አስርተ አመታት ሁለት የከሸፉ አብዮቶችን አስተናግዳ ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንክሮ ወደሚከታተለዉና ምናልባትም በታሪካችን የመጨረሻ ወደሆነዉ ስር ነቀል የለዉጥ ሂደት ዉስጥ ገብታለች።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አስርተ አመታት ሁለት የከሸፉ አብዮቶችን አስተናግዳ ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንክሮ ወደሚከታተለዉና ምናልባትም በታሪካችን የመጨረሻ ወደሆነዉ ስር ነቀል የለዉጥ ሂደት ዉስጥ ገብታለች።
ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአመታት በከፈለዉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተጀመረዉ የለዉጥ ሂደት አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የፍትህ፥ የነጻነት፥ የዲሞክራሲና የእኩልነት መሰረት መጣሉን ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሳ መሆኑን እና ይህንን ለማድረግ ደግሞ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በለዉጡ ሂደት ዉስጥ ለማሳትፍ ፈቃደኛ መሆኑን ባለፉት ሦስትና አራት ወራት የተጓዘበት መንገድ በግልጽ አሳይቶናል።
ይህንን ተከትሎ በጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራዉ መንግስት ያደረገዉን የሰላምና የአብረን አገራችንን እንገንባ ጥሪ ተቀብለዉ በዉጭ አገሮች የሚኖሩ አያሌ የፖለቲካ ድርጅቶችና ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አገራቸዉ ዉስጥ የተጀመረዉን የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ለማገዝ ወደ አገር ዉስጥ ገብተዋል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአመታት የታገልንለትን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ገንብተን የሰላምና የብልፅግና ኑሮ መኖር የምንችለዉ በመጀመሪያ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መረጋጋት የሰፈነባት አገር ስትኖረን ብቻ ነዉ የሚል ጽኑ እምነት አለዉ።
አርበኞች ግንቦት ሰባት እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአመታት የታገልንለትን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ገንብተን የሰላምና የብልፅግና ኑሮ መኖር የምንችለዉ በመጀመሪያ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መረጋጋት የሰፈነባት አገር ስትኖረን ብቻ ነዉ የሚል ጽኑ እምነት አለዉ።
ዛሬ ሁላችንም በግልጽ እንደምንመለከተዉ በመፍረስ ላይ ካለዉ ስርአት የተወረሱ አንዳንድ ተቋማዊ ችግሮች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ለረጂም ዘመን አብሮ የኖረን ህዝብ እርስ በርሱ ሲያጋጩና ደም ሲያፋስሱ እየተመለከትን ነዉ።
አርበኞች ግንቦት ሰባት እነዚህ ችግሮች የሁላችንም ችግሮች ናቸዉና የኢትዮጵያ ህዝብ፥ መንግስት፥የፖለቲካ ድርጅቶች፥ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አንድ ላይ በመምከርና የችግሮቹን መፍትሄ በመፈለግ ፍትህ፥ ነጻነት፥ ዲሞክራሲ፥ እኩልነት፥ ሠላም እንዲሁም ዕድገትና ብልፅግና የተረረጋገጠባትን ኢትዮጵያ ለሚቀጥለዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን አንድ ላይ እንስራ የሚል አገራዊና ወገናዊ ጥሪ እያስተላለፈ አዲሱ አመት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ድል የምናስመዘግብበት የሠላምና የድል አመት እንዲሆንልን ምኞቱን ይገልጻል።
አንድነት ሀይል ነዉ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ
መስከረም 19 2011 ዓ.ም
አንድነት ሀይል ነዉ!!!
አርበኞች ግንቦት 7፣ ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ ንቅናቄ
መስከረም 19 2011 ዓ.ም
0 Comments