ከመወቃቀስ ፖለቲካ እንውጣ!! (አዲስ መኮንን)

ከመወቃቀስ ፖለቲካ እንውጣ!!
ወቀሳው በዚህም በዚያም እየተፋፋመ ነው፡፡ አንዱ አንዱን ወቃሽ ሆኗል፡፡ አንዳንዶች ችግሩ ሲከሰት ትንፍሽ ሳይሉ ዛሬ ብቅ ብለው ጥፋተኛው እከሌ ነው፤ ስልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ነው እትት… ማለት ጀምረዋል፡፡

መጀመሪያ ሁለት ፉርሽ የሆኑ ሃሳቦችን እዚሁ ገድለናቸው እንለፍ፡፡

  • ብጥብጡን ያስነሳው የአንድነቱ ጎራ ነው የሚለው ነው፡፡ 

ይሄ በጭራሽ "ለእውነት ትንሽ እንኳ ያልቀረበ" ይልቁንም "ከፍራቻ የመጣ ሃሳብ ነው" የሚመስለው፡፡ የአንድነት ሃይሉ ለብሄር ድርጅቶች እንቅፋት ፈጥሯል ተብሎ በሚወቀስበት ዛሬ ተነስቶ የብሄር ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል ብሎ ማውራት ትዝብት ውስጥ የሚከትም ነው፡፡

እንዲያውም የአንድነት ሃይሉ ከዶ/ር አብይ አስተዳዳር ጎን እንደተሰለፈ በይፋ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ይሄኛው መላምት ውድቅ ይሆናል፡፡

  • የተሸነፉ ሃይሎች ናቸው የሚባለው ነው፡፡ 
ይሄ ሄዶ ሄዶ ህወሃቶች ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ያለፈበት ፋሽን ነው፡፡ ይልቁንም እነሱ መቀሌ ላይ ከትመዋል፡፡ ከዚያ ውጭ አብዛኛውን ስልጣን ስላጡ ዛሬም ይህንን ያድርጋሉ ብሎ ማለት ‹‹ጨፍኑ ላሞኛችሁ›› ነው የሚሆነው፡፡ ህወሃት የምትለው መዝሙር ከአሁን በኋላ አትሰራም፡፡

ስለዚህ ይህ ግጭት ሌላ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ቀድመው የተወሰኑ ስህተቶች ኦነግን ለመቀበል በውጡ ሰልፈኞች ላይ ተፈፅሟል፡፡ የመጀመሪያው ከአመት በፊት ከቡራዩ አካባቢ ተፈናቅለው ጨረታ አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ሰዎች ቄሮ ለሰላማዊ ሰልፍ ወደ መስቀል አደባባይ ሲያመራ በተወሰነ መልኩ ድብደባ አድርሰውባቸው ነበር፡፡

ቄሮ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዳለም ቤታቸው ድረስ በመሄድ የተወሰኑ ዝርፊያዎችም ተፈፅሞባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚች እልህ የገቡት ቄሮች እርምጃ ወስደዋል፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ተዳብለው ሰፋ ያለ ግጭት ፈጥረዋል፡፡ ከዚያ ግን ታቅዶ ተደራጅተው የተቀመጡ ሰዎች ብዙ ጥፋት አጠፉ፡፡ ሰዎች ተገደሉ ተፈናቀሉ፡፡

ትልቁ ነገር ያለው እነዚህን ሰዎች ማን አደራጅቶ አስቀመጣቸው የሚለው ነው፡፡
አንድ ሰው ለኢሳት ሲገልፁ እንዚህ የተደራጁ ሰዎች በፖሊስ ሁላ እንደሚፈሩና የሆነ አካል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተናገረዋል፡፡ ይሄንን አጥንቶ መድረስ ይጠይቃል፡፡ ከጀርባ አንዳች ነገር መኖሩ እሙን ነው፡፡

ከዚያ ውጭ የኦሮምያ ፖሊስ ጥቃቶች ሲፈፀሙ እና ንብረት ሲዘርፍ የመከላከል እርምጃ አልወሰደም፡፡ አንዳንዶች ምክንያታቸው ምንድነው ብለው ሲጠይቁ ትዕዛዝ አልተሰጠንም የሚል መልስ እንደመለሱላቸው ሰምተናል፡፡

ሰላም ማስጠበቅ በትዕዛዝ የሚፈፀም አይመስለኝም፡፡ የፖሊስ የመጀመሪያ ስራ ወንጀል እንዳይፈፀም ቀድሞ መከላከል በመሆኑ፡፡ ሌላው ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳው ጉዳይ ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ በማህበራዊ ድረገፆች በሰፊው የተዘመተበት የሽግግር መንግስት ይቋቋም ጥያቄ ዘመቻ ነው፡፡ ይሄ ለምን በዚህ ሰዓት ተፈፀመ፡፡

ሶስት መላ ምቶችን እናስቀምጥ!

  • ኦነግ በአብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ እንደ ገዳይና አራጅ ተደርጎ እንዲሳል የተደረገ ድርጅት ነው፡፡ 
ለኦሮሞ ህዝብ ደግሞ እንደ ትልቅ የነፃነት አጋር ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ ባለፉት አመታት በድርጅቱ ላይ የተነዛው ‹‹ተገንጣይ ነው›› የሚለው ፕሮፖጋንዳ ተጨምሮብት በ1983 በአማራ ህዝብ ላይ (በእጅ አዙርም ይሁን በምን) የፈፀመው ጥፋት በሌሎች ዘንድ እንደ አውሬ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

ዛሬ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ ያንን ወቅት ለማስታወስና ‹‹ አንዳልናችሁ ኦነግ ከመግደል ውጪ ስራ የለውም›› ለማስባል የተሸረበበት ሴራም ሊሆን ይችላል፡፡ ሸራቢውን ግን እግዝሬ ይወቀው፡፡ መላምት ለማስቀመጥ አይመችም፡፡
  • በኦነግ አቀባበል ላይ የአዲስ አበባ ህዝብ ብዙም ትኩረት ሰጥቶት የተሳተፈ የለም ማለት ይቻላል፡፡ 
ኦነግ ይቺን ሲያይ አዲስ አበባ ላይ በምርጫ እንደማያሸንፍ ስለሚያውቅና አርበኞች ግንቦት ሰባት ደግሞ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው በመረዳቱ ግንቦት ሰባትን በአዲስ አበባ ህዝብ ለማስጠላት ቡራዩ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማቀነባበር በግንቦት ሰባት ማላከክ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ትዕዛዝ የተሰጣቸው ይመስል ግንቦት 7 ላይ በዚህ ጉዳይ ሲዘምቱ ነበር፡፡
  • አብዛኛው ሰው በዶ/ር አብይ አስተዳደር ጉያ በመግባቱ 
ብዙሃኑ ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ማበሩና ብዙ ድጋፍ በመስጠቱ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለብሄር ድርጅቶች ጀርባውን መስጠቱ እንደ አብይ ያለው አስተዳደር አያዋጣህም በዘርህ ብትደራጅ ይሻልሃል ለማለትም ብሄርተኞች ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የሚሉ መላምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ሲጠቃለል
አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት የእኛ ሀገር ፖለቲካ የሸፍጥ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህንን ከላይ የጠቀስኳቸውን ሴራዎችም እንኳ እንዳስቀምጥ ያደረገኝ የሸፍጥ ፖለቲካው አስተምሮኝ ነው፡፡ አንዱ አንዱን ገድሎ በሬሳ ላይ በመረማመድ ስልጣን ለማግኘት የተጠናወተን አባዜ ዛሬም የለቀቀን አይመስልም፡፡

ዛሬ እድል ገጥሞን በሰላማዊ መንገድ መጥታችሁ ታገሉ፤ በአፈ ሙዝ ሳይሆን ምርጫ በካርድ አሸንፋችሁ ስልጣን ያዙ የሚል መሪ እና መንስግስት አግኝተናል፡፡

በሴራ ግድያና ማፈናቀል ውስጥ ምን ወሰደን?
የሰው ነፍስ ዋጋው ስንት ነው? እስከመቼ እንደዚህ በንፁህን ነፍስ ላይ እንቀልዳለን? መቼስ ነው ሰው ስለሆኑ ብቻ ሰብዓዊ መብታቸውን እናክብርላቸው/ይከበርላቸው ብለን የምንጮኸው? አሁን ጥሩ እድል አለን፡፡ እድሉን መጠቀም ካልቻልን መከራችን መርዘሙ ነው፡፡

ጥፋቶች ሲታየው የፖለቲካውን ንፋስ አነፋፈስ በመተው ለህሊናቸው የሚቆሙ የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል፡፡

ብሄር የማይቆጥሩ እምነት የማያዩ ለሰብአዊነት ብቻ የቆሙ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ እንደ አርባ ምንጮቹ አባቶች ቄጤማ ይዘው የተቆጣን ከቁጣው የሚመልሱ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡

መንግስትም እየተከተለው ያከው ፍልስፍና የሚደገፍ ቢሆንም እዚያ ፍልስፍናላይ ያልደረሱ ሰዎች ወይም ደግሞ መድረስ የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝቦ አንዳንድ አካሄዶችን ጠንከር ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ከዚያ ውጪ ግን በሰሞኑ ነገር ብቻ የኦሮሞን ህዝብ በጅምላ ለመፈረጅ መሞከር ትልቅ ጥፋት፡፡
እውነት ነው ከውስጡ የወጡ በዘረኝነት ያበዱ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ አለ፡፡

ነገር ግን ህዝቡ እንደህዝብ ደግ ህዝብ ነው፡፡
ድሮ ድሮ በብሄሮች እንኳ ሲቀለድ የኦሮሞ ህዝብ የደግነትና የየዋህነት ውክልና ነበር የሚሰጠው፡፡

ይህንን እየተባልን ላደግን ሰዎች ዛሬ መጥታቸው የኦሮሞን ህዝብ በጅምላ ብትፈርጁ አንቀበላችሁም፡፡
የትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ አረም ሞልቷል!
ከዚያ ውጭ በቡራዩው ጥቃት አንድ የደቡብ ሰው አንድ ኦሮሞ ቤቱ ቆልፎበት ነፍሱን እንዳተረፈለት ተናግሯል፡፡

በትንሹ ይቺን እንኳ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚያ ውጭ ውጭ አክቲቪስት ተብየዎቹን እንዝለላቸው፡፡ ሲያራርቁን እንጂ ሲያቀራርቡን አላየንም ፡፡

Post a Comment

0 Comments