የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የተመለከቱና ሌሎች አጫጭር ዜናዎችን ያንብቡ - ቢቢሲ


አፍሪካ
• በባሌ ዞን ጎለልቻ ወረዳ፤ ቡላላ ሃረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር በጸጥታ ሃይሎችና በአርሶ አደሮች መካከል በተከሰተ ግጭት የአምስት አርሶ አደሮች ህይወት ሲያልፍ አስሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ግጭቱ ለኢንቨስትመንት የተሰጠ መሬት ይገባናል በሚል እንደተነሳ የወረዳው ምክትል ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አብዱራህማን ሼክ ከድር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

• የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኬንያ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ዛሬ ረፋዱ ላይ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምድ ሰርቷል። የኬንያው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ሊከብዳቸው እንደሚችል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

• ታዋቂዋ ኬንያዊት ዜና አንባቢ ጃኪ ማሪቤ እና እጮኛዋ የአንዲትን ሴት ህይወት በማጥፋት ተከሰሱ። የኬንያ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ እንዳስታወቀው ''ሲቲዝን ቲቪ'' በተባለው የቴሌቪዥን ጣብያ የምትሰራው ሴት የአእምሮ ህመም ምርመራም እየተደረገባት ነው።

• ማንነቱ ያልተጠቀሰ ደቡብ አፍሪካዊ በአንድ የካቶሊክ ቄስ ለብዙ ዓመታት ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰበት ገለጸ። በ13 ዓመቱ የጎዳና ላይ ታዳጊ ሳለ ቄሱ ልርዳህ ብለው እንደቀረቡትም ተናግሯል።

• ሴኔጋል የ2022ቱን የክረምት ወጣቶች ኦሎምፒክ ልታዘጋጅ ነው። የአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዳስታወቀው ውድድሩን ለማዘጋጀት ቦትስዋና፣ ናይጄሪያና ቱኒዚያ ከሴኔጋል ጋር ተፎካክረው ነበር።

አሜሪካ
• በአሜሪካና ቻይና መካከል ያለው የንግድ ጦርነት አለምን ወደ ከፋ ድህነት እና ችግር ሊከታት እንደሚችል አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ አስጠነቀቀ።

ተቋሙ በቅርቡ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት በያዝነውና በቀጣዩ ዓመት የአለም ኢኮኖሚ እድገት ሊቀንስ እንደሚችልም አስቀምጧል።

• በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄይሊ የስራ መልቀቂያ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ማስገባታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

አምባሳደሯ እስከ ያዝነው ዓመት መጨረሻ ድረስ በሃላፊነት እንደሚቆዩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

• በሜክሲኮ ኤካቴፔክ በምትባል ትንሽ መንደር የሚኖሩ ባልና ሚስት የሰው ልጅን አካል ላልታወቁ ሰዎች ይሸጡ እንደነበር ፖሊስ ገለጸ።

ፖሊስ ባልና ሚስቱ ከሚኖሩበት አፓርትመንት በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቤት ያስቀመጧቸውን የሰውነት ክፍሎችን በብዛት አግኝቷል።

እሲያ
• የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን የቫቲካኑ ጳጳስ ፍራንሲስ ሃገራቸውን እንዲጎበኙ ግብዣ አቀረቡ። የትኛውም ጳጳስ ሰሜን ኮሪያን ጎብኝቶ የማያውቅ ሲሆን፤ ሁለቱ ሃገራት ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላቸውም።

• በጃፓን የእንስሳት ማቆያ ውስጥ የነበረ አንድ በመጥፋት ላይ ያለ ብርቅዬ ነብር ተንከባባቢውን ነክሶ ገደለ። የ40 ዓመቱ የእንስሳት ተንከባካቢ አንገቱ ላይ በደረሰበት ንክሻ ነው ህይወቱ ያለፈው።


Post a Comment

0 Comments