ከአርበኞች ግንቦት 7 የተሰጠ መግለጫ
አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡ ከአርባ ቀን በኋላ እና በመጀመሪያ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለብዙ ቀናት ቀጥሎም ምክር ቤቱ ከአንድ ሳምንት በላይ የፈጀ ስብሰባ ከተቀመጠ በኋላ ዶ/ር አቢይ አህመድን የግንባሩ ሊ/ቀመንበር አድርጎ መርጧል። የዶ/ር አቢይ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆኖ መመረጥ የሚቀጥለዉ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላል በሚል በአትኩሮት ሲጠበቅ ለነበረው ጥያቄ የመጀመሪያ ዙር ምላሽ ሰጥቷል።
ለመሆኑ የዶ/ር አብይ መመረጥ የተለመደው የወያኔ የሴራ አካሄድ ውጤት ነዉ? ወይስ ኢህአዴግ የህዝብን እውነተኛ የለውጥ ፍላጎት ሰምቶ መንገዱን ለማስተካከል የወሰደዉ ዕርምጃ ነዉ? የኢህአዴግ ዉሳኔ እነዚህን ጥያቄዎች ያጠቃለለ ጥልቅ ውይይት ተካሂዶበት የተወሰነ መሆኑንና ያለመሆኑን በቅርቡ የምንሰማውና በተግባርም የምናየው ይሆናል።
የዶ/ር አብይ መመረጥ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት እስካሁን የህወሀት ሎሌ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ድርጅቶችና በህወሓት ውስጥም ያሉ አንዳንድ ለውጥ ፈላጊዎች በጋራ አሸንፈው ከሆነና እነ ዶ/ር አብይ በተለይ በኦህዴድ ምክር ቤት ስብሰባ መግለጫ ላይ ያወጡትን ለውጥ ፈላጊ አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነው ከሆነ እሰየው ነው። የኢህአዴግ ዉሳኔ በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል፥ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ብሎም ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለውጥ ፈላጊው ህዝብ ሁሉ የሚፈልገው ነውና በአዎንታዊ መልኩ የምንወስደው ነው።
ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆነዉ የተመረጡት ኢትዮጵያ በከፍተኛ የለውጥ ማዕበል በምትናጥበትና መብቴና ነጻነቴ ይከበር ብሎ የሚጮህ ህዝብ በየአደባባዩ በሚገደልበት ወቅት ስለሆነ ከዶ/ር አቢይ ተቀዳሚና ዋና ዋና ሃላፊነቶች ዉስጥ አንዱ ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ዉስጥ የተረጋጋች አገር እንድትሆን ማድረግና የህዝብን የመብት፥ የፍትህና የነጻነት ጥያቄዎች መመለስ መሆን አለበት ብሎ አርበኞች ግንቦት ሰባት በጥብቅ ያምናል።
ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት ኢህአዴግ ዉስጥ በለውጥ ፈላጊና “ያለዉ ይበቃናል” በሚሉ ሀይሎች መካከል ከፍተኛ ወስጠ-ፓርቲ ትግል ሲካሄድ እንደቆየ ሁላችንም ስንሰማዉ የቆየ ጉዳይ ነዉ። የዶ/ር አቢይ መመረጥ ይህ በሁለቱ ሀይሎች መካከል የተካሄደዉ ትግል በለዉጥ ፈላጊ ሀይሎች ድል መደምደሙን የሚያመለክት ከሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት ሊመጣ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታልና በሂደት የሚታይ መልካም አዝማሚያ ነዉ።
በሌላ በኩል ግን የዶ/ር አቢይ ማሸነፍ እንደተለመደዉ በህወሓት አጋፋሪነት የተመራና ለገዢዉ ፓርቲ የመረጋጊያ ግዜ ለመግዛት የተደረገ ሴራ ዉጤት ከሆነ የህዝብ ተመራጮች ነን የሚሉ የኢህአዴግ አባላት የህዝብን ትክክለኛ ፍላጎትና ጥያቄ በፍጸም አልተረዱም ማለት ነዉ። ህዝብ “በህወሓት መገዛት” ይብቃ፤ አምባገነንነት ይብቃ፤ የህዝብ መብት ይከበር፤ ህዝቡ በመረጠው መንግሥት ይተዳደር እያለ የህይወት መስዋዕትነት በሚከፍልበት ወቅት የህዝብ ተወካዮች የህወሓትን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት መሯሯጣቸዉ የህዝብ ጠላት እንጂ የህዝብ ተወካዮች ሊያሰኛቸዉ አይችልም።
ከላይ እንደተጠቀሰዉ ዶ/ር አቢይ የግንባሩ ሊ/መንበር ሆነዉ ሲመረጡ የአገሪቱም ጠ/ሚኒስትር ሆነዉ መመረጣቸዉን የሚያመለክት ስለሆነ አገሪቷ ወዴት መጓዝ እንዳለባት የሚጠቁም አቅጣጫ ስልጣኑን ከተረከቡ እለት ጀምሮ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት የመጀመሪያ ስራቸዉ መሆን አለበት። ይህ አቅጣጫ የማሳየት ስራ ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ቢሆንም ከዚህ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናችዉ :-
- ጓዳችንን አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍታት
- ህገ-ወጡን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማንሳት
- በህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በአስቸኳይ ማስቆምና ለዚህ ዕርምጃ ዋስትና እንዲሆን የአገሪቱን የደህንነት ተቋሞች እንደገና በአዲስ መልክ ማዋቀር
- የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንዲታገዱ ያደረጋቸዉና አዋጁ ከመታወጁ በፊትም ቢሆን በፍጹም ተከብረዉ የማያዉቁትን መደራጀትን፥ መሰብሰብን፥ መቃወምን፥ ሃሳብን በነጻነት መግለጽንና የህግ የበላይነትን የመሳሰሉ መሠረታዊ የሰዉ ልጅ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ
- ኢትዮጵያን ወደ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መውሰድ የሚችል ሁሉን አቀፍ ውይይትና የሽግግር ሂደት በአስቸኳይ ማስጀመር፥
አርበኞች ግንቦት ሰባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝብ የሚፈልገዉ ለዉጥ በተለያየ መልኩ ሊመጣ እንደሚችልና ለውጥ ከየትም ይምጣ ከየት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን በደስታ እንደሚቀብል በተደጋጋሚ ገልጿል፥ ይህ እምነታችንና ፍላጎታችን አሁንም የጸና ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ከእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ውጭ የሆነ ምንም አይነት ጥገናዊ ለውጥ እንደማይቀበልም በተደጋጋሚ ግልጽ አድርጓል።
የዶ/ር አቢይን አህመድን መመረጥም የምናየዉ ከዚሁ አኳያ ነዉ። ዶ/ር አቢይና ኢህአዴግ ዉስጥ የሚገኙ የለዉጥ አራማጅ ሀይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ መመለስ የሚጀምሩ ከሆነና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት ለመጀመር እጃቸዉን ለሁሉም የሚዘረጉ ከሆነ አርበኞች ግንቦት ሰባት ይህንን የለዉጥ ሂደት ይደግፋል፥ ለዉጤታማነቱ ይታገላል። ይህ በአንዲህ አንዳለ ግን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚወስደን የሽግግር ሂደት ተጀምሮ ህዝባዊ ትግሉ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱ እስከሚረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረዉን የፍትህ፥የነጻንትና የዲሞክራሲ ትግል ለአንድም ቀን ቢሆን እንዳያቆም አርበኞች ግንቦት ሰባት በጥብቅ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
0 Comments